• Thu. Mar 23rd, 2023

የብልፅግና መንግሥት የሰውን ልጅ በህይወት እንዲቃጠል በማድረግ ለፈፀመው አረመኔያዊ ድርጊት ከተጠያቂነት አያመልጥም። (የኦነግ-ኦነሠ ጋዜጣዊ መግለጫ)

Mar 14, 2022

የብልፅግና መንግሥት የሰውን ልጅ በህይወት እንዲቃጠል በማድረግ ለፈፀመው አረመኔያዊ ድርጊት ከተጠያቂነት አያመልጥም።

(የኦነግ-ኦነሠ ጋዜጣዊ መግለጫ)

ከመጋቢት 11 ቀን 2022 ጀምሮ የዶ/ር አብይ አህመድ መንግሥት የጸጥታ ሃይሎች እና ተባባሪዎቻቸው ወገኖቻችንን በህይወት እያሉ በእሳት ሲጠበሱ የሚያሳይ የአምስት ደቂቃ ቪዲዮ በየሚዲያ አውታሮች በሀገር ውስጥና ውጪ ወጥቶ ተመልክተናል:: ይሄ ከማሳዘንና ከማናደድም አልፎ ስነልቦናችንን ረብሾታል። ይህ አሰቃቂ የድንጋይ ዘመን አረመኔነት ሰው መሆን ምን ማለት እንደሆነ ለማወቅ ብዙ ያልተለመዱ ጥያቄዎችንም በብዙዎች ዘንድ አስነስቷል። የቪድዮውን አጠቃላይ እይታ መዘርዘር ቀላል ስራ ካለመሆኑም በላይ ማንም ጨዋ ሰው ዓይኑን ሞልቶ አይቶ ሊጨርሰው የሚችል አይነት ተግባር ግን አይደለም። ለተጎጂዎች እጅግ ልባዊ ሀዘናችንን በቅድሚያ እንገልፃለን!

ከሁሉም በላይ የሚያስጨንቀው ደግሞ ይህ አረመኔያዊ ድርጊት በመንግሥት የጸጥታ ሃይሎች እና በሰላማዊ ህዝብ ፊት መፈጸሙ ነው። በርግጥ ወንጀለኞቹ ጤነኛ የሰው ልጆች መሆናቸውን ለማመን አስቸጋሪ ቢሆንም፣ ከዚህ የተለየ ለማመን ግን ምንም አሳማኝ ምክንያት የለም። በትክክለኛው የሰው ልጅ አኗኗር ወንጀለኞቹ የሰው ልጅ ጎረቤቶች: እድር ያላቸው በሰው ልጅ ደስታና ሀዘን የሚሳተፉ ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ከዚህ አንፃር በኢትዮጵያ እንዲህ ዓይነቱ ጭካኔ መቼ እንዴትና ለምን እንደተለመደ በጥልቀት መመርመር አለበት እንላለን።

ኦነግ-ኦነሠ ግን በቪዲዮው ላይ በሚታዩት ወንጀለኞች ማንነት ላይ ያተኮረ የተሳሳተ ትኩረትና ድምዳሜ መስጠትን አይቀበልም። እነዚህ ወንጀለኞች በብልጽግና ፓርቲ እና በአማራ ጽንፈኛ ሀይል አጋሮቻቸው በኦሮሚያ፣ በትግራይ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በቅማንት፣ በአገው፣ በአፋር፣ በጋምቤላ፣ በሶማሊ፣ በሲዳማ፣ ወዘተ ህዝቦች ላይ የታወጀው የዘር ማጥፋት ፕሮጀክት ፈፃሚዎች ብቻ ናቸው። እነዚህ አሰቃቂ ወንጀሎች ከጽንፈኛው የአማራ ልሂቃን ዲስኩርና የመስፋፋት ፖሊሲ ጋርም በቀጥታ ይገናኛል ። በተለይም ፍፁም ሰላማዊውን የሰው ልጅ ወደ እንስሳነት የሚቀይሩ መጥፎ ንግግሮችና ዲስኩሮች በቅርብ ጊዜ በአደባባይ ወጥተው መነገራቸውን ማየት ይህን በአግባቡ እንድንረዳው ያደርገናል::

ለረጅም ጊዜ እንደምናውቀው የአማራው ተስፋፊና ፅንፈኛ ሀይል በፊንፊኔ የተማከለውን ስልጣናቸውን የሚቃወምና ብሎም የሚደፍርን የሰው ልጅ በዚሁ አይነት አሰቃቂና ሰይጣናዊ መንገድ ሲቀጡ ቆይተዋል። የአሁኑን ልዩ የሚያደርገው በመረጃ ዘመን ከመኖራችን የተነሣ መደበቅ ያለመቻላቸው ብቻ ነው:: ኦሮሞዎች፣ የትግራይ ተወላጆች፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ የቅማንት፣ የአገው፣ የአፋር፣የሶማሌ፣ የጋምቤላ፣ የሲዳማ እና ሌሎችንም ህዝቦች ደረጃው ቢለያይም የዚህ ሰይጣናዊ ድርጊ ሰለባዎች ነበሩ:: ዛሬም ናቸው። የቅርብ ጊዜውን ብቻ ብንወስድ፣

በአማራ ከፍተኛ የፖለቲካ መሪዎች እና ቱጃር ነጋዴዎች በኩል ሲታወጁ የነበሩ ሰይጣናዊ ንግግሮችንና ቅስቀሳዎችን እንደምሳሌ ማየት በጣም አስፈላጊ ነው።

የገዥው የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አማካሪና ኢሳት ስራ አስፈፃሚ የሆነው አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በአማራ ክልል ለተሰበሰበ ህዝብ እንዲህ ብለው ነበር::

“ለእነሱ (ለትግራይ ተወላጆች) ምንም አይነት ምህረት ልታሳዩአቸው አይገባም። የኛ ባህል ከሚፈቅደው በላይ መጨከን አለባችሁ። በሚያስገርም አረመኔያዊ ጭካኔ ልትዋጓቸው ይገባል።” ነበር ያለው::

የአማራ ቢሊየነር እና የብልፅግና ፓርቲ የቅርብ አጋር የሆነው አቶ ወርቁ አይተነው በበኩሉ በአደባባይ እንዲህ ብሎ ነበር።“እነሱን (የትግራይን ህዝብ) መግደል ብቻውን በቂ አይደለም። እንደ ፍየል ሥጋ ቆራርጠህ ጠብሰህ መብላት ነው።” ነበር ያለው:: በኛ በኩል ይህ አባባል የሚፈጠርበትን አእምሮ በላቀ ደረጃ መመርመር የሚያስፈልግ ይመስለናል:: እንዴት ሆኖ የሰው ስጋ ተቆራርጦ ከሚጠበስ የፍየል ስጋ ጋር ተመሳስሎ ታየው? ቀድሞ አድርጎት ያውቅ ይሆን እንዴ? የሚል ጥያቄም ያጭራል::

ለማንኛውም እንዲህ አይነቱ ሰይጣናዊ የአደባባይ ዲስኩሮች የኢትዮጵያን ስም እየተሸፈኑ በጽንፈኛ የአማራ ልሂቃን የሚቀርቡ የተለመዱ ግን አደገኛ ንግግሮች መዘዛቸው የከፋ መሆናቸውን ማወቅ ተገቢ ይሆናል።

በሀገሪቱ ውስጥ ከኦሮሞ፣ ከትግራይ ወይም ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች የፖለቲካም ሆነ የባህል መሪዎች እነዚህን የአብይ አህመድ አጋር የአማራ ጽንፈኞች ንግግር የሚመሳሰል ፀያፍና አደገኛ ንግግር በፍፁም ተሰምቶ አያውቅም።

ስለዚህ የሰው ልጅን በእሳት ያቃጠሉትና እና አሰቃቂ ተግባራቱን የፈፀሙት እጆች ማንም ይሁኑ ማን ምንጩና አስፈፃሚው ከፖሊሲው፣ ከንግግሮቹ፣ እንዲሁም ከወታደራዊ አዛዦቹ መሆናቸውን መጠራጠር አይገባም:: ይህ ክስተት “አጸያፊ ንግግሮች ሰዎችን ወደ አውሬነት የመቀየር ሀይል አላቸው” ለሚለውና በሌላ በኩልም “የማይረባ ነገር እንድታምን የሚያደርጉህ ሰዎች የማይታመን ግፍ እንድትፈጽምም ሊያደርጉህ ይችላሉ” ለሚሉት አባባሎች ትክክለኛነት ማረጋገጫ ነው።

በአብይ አህመድ ኢትዮጵያ እንደዚህ አይነት እኩይ ተግባር እየተለመደ መሆኑ ከማንም የተሰወረ ባለመሆናቸው ደጋግመን እንደገለጽነው የብልጽግና ፓርቲ እና አጋሮቹ ለሚፈጸሙት ጥፋት ሁሉ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊትን ተጠያቂ ማድረጋቸውን እንደቀጠሉ ነው። ብልፅግና በቅርቡ 5000 የሚጠጉ ኦሮምኛ ቋንቋ የሚናገሩ ቅጥረኞቹን በሰንቀሌ ፖሊስ አካዳሚ ውስጥ በማሰልጠን ተመሳሳይ አሰቃቂ ወንጀሎችን እንዲፈጽሙ ኦሮሚያና አጎራባች ቦታዎች ላይ አሰማርቷል።

በኛ በኩል፡-

1ኛ) የአብይ አህመድ እና የአማራ አክራሪ አጋሮቹ በህዝብ ላይ በጂምላና በተናጠል ለሚደረሱ ግፍና ጭፍጨፋዎች በቀጥታ ተጠያቂ መሆናቸውን:-

2ኛ) በኦሮሚያ ክልል እነዚህ ሀይሎች በፈፀሙት ግፍ የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊትን ለመክሰስ ተመሳሳይ ወንጀል ሲሰሩ መቆየታቸውን:-

3ኛ) በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ኦሮሞዎችን እና መጤ ነዋሪዎችን ለመጨፍጨፍና እና ለማፈናቀል አሁንም ተጨማሪ የኦሮምኛ ቋንቋ የሚናገሩ ቅጥረኞችን በማሰልጠን አሰማርቶ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊትን ለመክሰስ ማቀዱን የሚያሳይ ማስረጃ በበቂ ሁኔታ አለን። ጊዜው ሲደርስም ለህዝብ እናቀርባለን:: ለዚህም ህዝቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ እና የዚህ አይነት ግፎችን የሚፈፅም ሀይል ሲገኝ በውል ለምታውቁት የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት አሀዶች በመጠቆም ደህንነታችሁን እንድትጠብቁ እናሳስባለን::

ፍትህ ለተጎጂዎች!

ድል ለኦሮሞ እና ለተጨቆኑ ህዝቦች በሙሉ!

የኦነግ-ኦነሠ ከፍተኛው ዕዝ

ማርች 14፣ 2022

Leave a Reply