• Sat. Sep 23rd, 2023

በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የቀረበን የሰላም ጥሪ በሚመለከት (የኦነግ-ኦነሰ መግለጫ)

Feb 28, 2023

የካቲት 10 ቀን 2015 ዓ/ም የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት ለክልሉ ምክር ቤት (ጨፌ)  ባደረጉት ንግግር የእርቅ ጥሪ አቅርበዋል።  የኦሮሞ ነፃነት ግንባር-የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት (ኦነግ-ኦነሰ) ገና ከጅምሩ በኦሮሚያ ውስጥ ያለውን ጦርነት በውይይት እና ድርድር  እልባት እንዲገኝ ያለው ዝግጁነት የማያወላውል መሆኑን በየጊዜው አቋሙን እየገለፃ የቆየ ሲሆን፥ በቅርቡም ባወጣው አጭር የፖለቲካ መግለጫ (ማኒፌስቶ) ይህንኑ በድጋሚ አመላክቷል። ኦነግ-ኦነሰ የኢትዮጵያን ውስብስብ የፖለቲካ ችግሮች ለመፍታት እና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚቻለው ሁሉን አቀፍ (comprehensive) በሆነ የፖለቲካ ውይይት እና ድርድር በማድረግ ብቻ እንደሆነ በጽኑ ያምናል። በመሆኑም፣ ኦሮሚያ ላይ እየተቀጣጠለ ያለው ጦርነት እንዲቆም እና በሰለጠነ ንግግርና ድርድር እንዲፈታ የሚቀርብ ማንኛውም ጥሪ በአዎንታዊ ጎኑ የምንቀበለው ጉዳይ ነው።
ነገር ግን፣ የሰላሙ ጥሪ በኦሮሚያ ሊመጣ ያለውን የሰላም ሂደት በተመለከተ ኣስፈላጊው ግልፀኝነት የሚጎድለው እና በእርቅ ሂደት አጀማመርም ላይ ከልክ ያለፈ ተስፈኝነት የሚታይበት ሆኖ አግኝተነዋል። የኢትዮጵያ መንግስት ይህን መሰል የሰላም ጥሪ ሲያቀርብ ይህ የመጀመሪያው ኣይደለም። በመደበኛ እና መደበኛ ባልሆነ መልኩ ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው የሰላም ጥሪዎች ለበርካታ ጊዜያት ሲቀርቡ ቆይተዋል። የአሁኑም ጥሪ በቅርፅም ሆነ በይዘት አዲስ አይደለም። ከዚህ ቀደም ከቀረቡት ጥሪዎች የተለየ አይደለም። በቀጣዮቹ ቀናት ሊወጡ የሚችሉ ዝርዝር ነገሮች እየተጠበቁ ቢሆንም፣ እስካሁን ድረስ ባለው፣ ጥሪው የባለፉትን የሰላም ጥሪዎች ክመደጋገም ያለፈ ሆኖ አላገኘነውም።
በእኛ በኩል፣ ማንኛውም የሰላም ሂደት ገና ከጅምሩ ግልጽ ማድረግ ከሚገባቸው ቁልፍ ነጥቦች ውስጥ በሚከተሉት ላይ ማተኮር እንፈልጋለን።
1. የኢትዮጵያ መንግስት በኦሮሚያ የተከሰተውን ግጭት አሳሳቢነት ሆነብለው ዝቅ በማድረግ ድርድሩም በደረጃ-2 (track-II) እርከን እንድቀርብ በማድረግ ወደ የሀገር ውስጥ ሽምግልና ለማዛወር ሲሞክር ይታያል።  ነገር ግን፣ ኦነግ-ኦነሰ ይህንን ዘዴ እና አካሄድ በማያሻማ ሁኔታ በሚከተሉት ምክንያቶች ውድቅ ያደርገዋል፣

ሀ) ዛሬ ባለው ዋልታ በረገጠ የፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ፣ ገለልተኛ አስታራቂ ከሀገር  ውስጥ ማግኘት በቀላሉ የሚታሰብ ነገር አይደለም። ምንም እንኳን በዕድል ብዛት ከስንት አንድ፣ በሁለቱም ወገኖች ተቀባይነት ያላቸው ገለልተኛ የሀገር ውስጥ አስታራቂ አካላት ቢገኙ እንኳን፣ ማንኛውም የአገር ውስጥ አስታራቂ አካል፣ አሁን በሀገሪቱ ዉስጥ ባለው ሁኔታ ከመንግስት ተፅእኖ ውጭ በገለልተኝነት መስራት  ይችላል የሚል እምነት ኦነግ-ኦነሰ የለውም።
ለ) ትርጉም ያለው ሽምግልና: ችሎታን፣ የሎጂስቲክ አቅርቦት እና ተዛማጅ መገልገያዎችን ማቅረብን ይፈልጋል። የኦነሰ አዛዦች እና ተደራዳሪዎች ከግጭት ቀጣና ወጥተው መግባት መቻል አለባቸው። ለዚህ የሚሆን መጓጓዣ፣አስፈላጊ የደህንነት ዋስትናዎች እና ሎጅስቲክስ ሊገኙ የሚችሉት በአለም አቀፍ አደራዳሪዎች ደረጃ ብቻ ነው።
ሐ) የሰላም ድርድሩ ውጤታማ እንዲሆን፣ የአደራዳሪዎች ሚና መደበኛ እና ገለልተኛ  የሆነ ሶስተኛ ሀገር በታዛቢነት በተገኘበት መደረግ አለበት፣ ከዚህ ያነሰ ነገር  ማድረግ የከሸፈውን በኦነግ እና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል የተደረገ የአስመራ ስምምነት መድገም ይሆናል።
መ) በሽምግልና ለተደረሰበት ስምምነት መተግበር በተወሰነ ደረጃ ዋስትና ሊሰጡ የሚችሉት የዓለም አቀፍ አደራዳሪዎች ብቻ ናቸው።ይህ በራሱ ወሳኝ መስፈርት ነው። በአለም አቀፍ ደረጃ እንኳን በጣት የሚቆጠሩ ሀገሮች ብቻ፣ ለስምምነቶች መተግበር ተገቢዉን ጫና መፍጠር ይችላሉ።

2. የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ክልሉን በሚያሳትፍ ሁኔታ የሰላም ሂደት አካል መሆን እንዳለበት ብንገነዘብም፣ ከኦነግ-ኦነሰ ጋር የሚደረገው የሰላም ሂደት ግን በፌዴራል መንግስት መመራት አለበት ብለን እናምናለን። ኦነግ-ኦነሰ በአሸባሪነት እንዲወነጀል ያወጀው የፌደራል ፓርላማ እንጂ የክልሉ ምክር ቤት አይደለም። በተግባርም እየታየ ያለው፣ ከኦነግ-ኦነሰ ጋር የሚካሄደውን ወታደራዊ ፍልሚያ እየመራ ያለው የፌደራል ሰራዊት እንጂ የክልል ሃይሎች ብቻ አይደሉም። ስለዚህ ከኦነግ-ኦነሰ ጋር የሚደረገው የሰላም ሂደት በህግም ሆነ በተግባር ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የስልጣን ወሰን እና አቅም በላይ ነው።

3. በቴክኒክ አግባብም ከታየ፣የአሁኑ የሰላም ጥሪ ለኦነግ-ኦነሰ የቀረበ አይደለም። የክልሉ ፕሬዝዳንት ዛሬም “ኦነግ-ሼኔ” የተሰኘውን የታጠቀ ምናባዊ ቡድን ይጠቅሳሉ። ይህ በይዘቱ ላይ ብዙም ለውጥ ባይኖረዉም፣ እንዲህ ያለው ፍረጃ፣ ቀደም ሲል የነበሩትን ፈርጀ ብዙ ችግሮች ከማባባስ በቀር ለሰላም ተስፋ ጋሬጣ እና ጥርጣሬዎችን የሚፈጥሩ ጉድዮች ለማጥራት እና የኢትዮጵያ መንግሥት የሰላም ሂደቱ አስመልክቶ  ሊከተለው የሚፈልገውን አካሄድ ግልጽ ለማድረግ አይረዳም።

ስለሆነም፣የኢትዮጵያ መንግሥት በኦሮሚያ የሚካሄደውን ጦርነት በሰላም እና በድርድር ለመፍታት ከልቡ የሚያምን ከሆነ፣ ተገቢውን አገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ መስፈርቶችን ለመከተል መስማማት አለበት የሚል አቋም አለን። እስካሁን በመንግስት እየተደረገ ያለው የሰላም ጥሪ ፣ በእኛ በኩል ለስሙም የሚመጥን ሆኖ ኣላገኘነዉም።

የኦነግ-ኦነስ የበላይ አዛዥ

ፌብሯሪ 18፣ 2023


Leave a Reply