• Wed. Nov 29th, 2023

የሰላም ድርድር እና የአገዛዙን የቅርብ ጊዜ ጥቃቶችን በተመለከተ (የኦነግ-ኦነሰ ጋዜጣዊ መግለጫ)

May 19, 2023

እ አ አ ግንቦት 3/2023 በታንዛኒያ የተደረገው የመጀመሪያው ዙር ውይይት ከተጠናቀቀ በኋላ፣ የአራት ኪሎው መንግስት በእኛ ጦር ቁጥጥር ስር ባሉ ይዞታዎች ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃቶች መፈፀሙን ቀጥሎበታል። ይህ እርምጃ በድርድር ሂደቶች ላይ ግጭቶችን ኣላማስፋፋት (de-escalation) ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል የሚለውን ግንዛቤ በእጅጉ ይቃረናል። በእኛ በኩል ይህ የአሁኑ ጥቃት፣ ሊኖር በሚችለው የሁለተኛው ዙር  ድርድር ላይ የተሻለ ጥቅም ለማስጠበቅ ሲባል ከወዲሁ ተሰልቶ የተነደፈ እቅድ መስሎ ይታየናል።

በመሆኑም፣ ምንም እንኳን ለሰላም ያለን ቁርጠኝነት በምንም ሁኔታ ውስጥ የማይናወጥ  ቢሆንም፣ በምዕራብ ወላጋ፣ በምስራቅ ወላጋ፣ በሆሮ ጉዱሩ፣ በምዕራብ ሸዋ፣ በምስራቅ ሸዋ፣ በአርሲ፣ በሃረርጌ፣ በቦረና እና ጉጂ ያሉ ይዞታዎቻችንን ለመከላከል የተገደድን መሆናችንን ሁሉም እንዲያውቀው እንፈልጋለን።

ይህ የመከላከል እርምጃ፣ በመንግስት አጥቂ ሀይሎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል። ኃይሎቻችን ግን፣ እያንዳንዱን የተቃጣባቸውን ጥቃት በተሳካ ሁኔታ በመመከት በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ያለውን የአገዛዙን ቀዳሚ የማጥቃት መሰናጃ እና መንደርደሪይ ቦታ በማውደም በቆራጥነት እና ውጤታማ በሆነ መንገድ የሚደነቅ መከላከል ኣሳይቷል።

ቢሆንም፣ ይህ ግጭት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚያደርሰው ጉዳት አሳሳቢ ነው። የአገዛዙ ኃይሎች የአስገዳጅ ስልቶችን በመከተል፣ የሲቪል ሰርቪስ ሰራተኞች ወታደራዊ ስራዎችን በገንዘብ እንዲደግፉ እና ገበሬዎች ለወታደሮቻቸው ምግብ እንዲያቀርቡ በማስገደድ ላይ ናቸው። የሚቃወሙት የቅጣት እርምጃዎች ይጠብቃቸዋል፣ ይህም ማዳበሪያን ከመከልከል እስከ ጅምላ ግድያ የሚደርስ የጭካኔ ትግባራትን ያጠቃልላል። ሰራዊቱ በግዳጅ ገበሬዎች የአካባቢው ሚሊሻዎችን እንዲቀላቀሉ ያደርጋሉ። የኦሮሚያን ከተሞችና መንደሮች ሲያቋርጡ የአገዛዙ ኃይሎች  በህዝቡ ላይ መጠነ ሰፊ ዘረፋ ያካሂዳሉ ፣ የሞባይል ስልኮቻቸው ይነጥቃሉ ፣ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ዘግናኝ ድብደባዎችን ይፈፅማሉ። በዝህም፣ እስካሁን ድረስ በርካታ ቤቶችን አቃጥለዋል፣ እርሻዎችን አወድመዋል፣ ፀያፍ እና ዘግናኝ የሆኑ ወሲባዊ ጥቃቶችንም ፈፅመዋል። እነዚህ እየተፈጸሙ ያሉ ግፎችና በደሎች አገዛዙ ለሰላማዊ ዜጎች ህይወት ያለውን ደንታ-ቢስነት አሳሳቢ ደረጃ መድረሱን ያሳያል። በተጨማሪም የሰላሙን ሂደት እንደ መልካም ኣጋጣሚ በመጠቀም፣ ሰላማዊ ዜጎችን በገንዘብ እየበዘበዙ  ከህዝባችን ያልተገባ ርኅራኄ ለማግኘት እየተንቀሳቀሱ ናቸው።

ምንም እንኳን፣ ህዝባችንን እና መሬታችንን ከማንኛውም ጥቃት ለመከላከል ባለን ቁርጠኝነት በጽናት ብንቆምም፣ ኦነግ-ኦነሰ ግን በወታደራዊ ግፊት የኦሮሞን የነፃነት እንቅስቃሴ ከሚገባው ድርሻ በታች የሆነን የፖለቲካ እልባት እንዲቀበል ማስገደድ እንደማይቻል ለማስገንዘብ ይወዳል። 

ስለሆነም፣ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አገዛዙ በወታደራዊ ሃይል የድርድርን ሚዛን ለመቆጣጠር የሚያደርገውን ሙከራ እንዲያወግዝ እናሳስባለን። አገዛዙም፣ ሁከትን ከማስቀጠል ይልቅ  ትርጉም ያለው ውይይት ለማድረግ ወደሚያስችል ሁኔታ ትኩረት እንዲያደርግ እና የሰማዕቶቻችንን የዘመናት መስዋዕትነት ባከበረ እና  የህዝባችንን የፖለቲካ ራዕይ በሚያሳካ ሁኔታ የተሟለ የፖለቲካ እልባት ሊያስገኝ በሚችል ድርድር ለመሳተፍ ራሱን እንዲያመቻች እንጠይቃለን። ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ብቸኛው አስተማማኝ መንገድ ይህ ነው ብለን እናምናለን!

ድል ለኦሮሞ እና ለመላው ጭቁን ህዝቦች !

የኦነግ-ኦነሰ ከፍተኛ አዛዥ
ግንቦት 19፣ 2023

Leave a Reply