የኦሮሞ ነፃነት ግንባር-ኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት (ኦነግ-ኦነሠ) ማዕከላዊ ኮሚቴ ከህዳር 28 ቀን 2024 እስከ ታኅሣሥ 6 ቀን 2024 መደበኛ ስብሰባውን ለዘጠኝ ቀናት አከሂዶ የተለያዩ ውሳኔዎች በማሳለፍ በስኬት እና በድል ተጠናቋል። በስብሰባው የድርጅቱ እንቅስቃሴ፣ የስራ ስነምግባር፣ የመዋቅርና በሠራዊቱ ውስጥ ያሉ ችግሮችን በዝርዝር ገምግሟል። በኦሮሚያ፣ ኢትዮጵያ፣ አፍሪቃ ቀንድ እና አለም አቀፍ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና ወታደራዊ ሁኔታዎችን በመተንተን ሊከተሏቸው የሚገቡ ስልቶችን እና ስትራቴጂዎችን በዝርዝር አስቀምጧል። ስብሰባው የኢትዮጵያ መንግስት በሀገሪቱ ህዝቦች ለይ በተለይም በኦሮሞ ህዝብ ላይ እያደረሰ ያለውን የፖለቲካ ጫና እና የሰብአዊ መብት ጥሰት በጥልቀት ተወያይቶበት የመፍትሔ አቅጣጫ ያስቀመጠ ሲሆን ለተግባራዊነቱም ለኦነግ-ኦነሠ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ትዕዛዝ አስተላልፏል።
የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት አዛዦች በ2018 እና 2019 በነፃነት ሠራዊቱ ላይ ተላልፎ የነበረውን ኢፍትሃዊ ውሳኔ በመቃወም፣ መስዋዕትነት የተከፈለበትን ዓላማ በመጠበቅ፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ዓላማን እና የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ኃይሉን በማሰባሰብ ፖለቲካዊ አደረጃጀቱን እና ሠራዊቱን በአንድ ላይ ኦነግ-ኦነሠ (ABO-WBO) በጥምረት በመምራት እና የኦነሠ ኃይልን በማጠናከር፣ ፊንፊኔ አፍንጫ ሥር በመንቀሳቀስ፣ በገጠርም በከተማም ጠላትን ፋታ በመንሳት የኦሮሞ ጥያቄ የበለጠ ተሰሚነት እንዲኖረው በማድረግ፣ ኢምፓየሪቱ የኦሮሞን ህዝብ ጥያቄ ተገዳ እንድታዳምጥ ያስገደደ ከመሆኑ የተነሳ በአለም አቀፍ ደረጃም ዲፕሎማሲያዊ እውቅና ተሰጥቶት ሶስተኛ ወገኖች በተገኙበት ድርድር እንዲካሄድ አስችሏል።
ኦነግ-አነሠ የኦሮሞ ህዝብ ለነፃነቱ እና ለሉዓላዊነቱ በሚያደርገውን ትግል እንደማይደራደር በተግባር አስመስክሯል። በተጨማሪም ኢምፓየሪቱ የኦሮሞን የፖለቲካ ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ዝግጁ እንዳልሆነች ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሲቀጥፍ የነበረዉን የሥራዓቱን ውሸት አጋልጧል። የኦሮሞ ህዝብን በጠመንጃ አፈሙዝ ለማንበርከክ እየገደለ እና እያፈናቀለ ያለውን አገዛዝ ከመታገል ጎን ለጎን የጦር ወንጀል እና የሰብአዊ መብት ጥሰት እየፈፀመ ያለው አገዛዝ የኦሮሞ ህዝብ መሰረታዊ ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ ለመመለስ መንገድ ካለው በራችን ክፍት መሆኑን በስብሰባው ውሳኔ በድጋሜ ተመልክቷል።
የኦነግ-ኦነሠ ማዕከላዊ ኮሚቴ በዚህ ውሳኔው፣ የሕዝባችን ጥያቄ ሊመለስ የሚችለው የኦሮሞ ኃይል፣ ከጥያቄው ጋር ተመጣጣኝ ከሆነ ብቻ መሆኑን ተረድቶ፣ በትግል ሜዳ ያለውን የትጥቅ ትግሉን አጠናክሮ፣ በወታደራዊ፣ በፖለቲካ፣ በዲፕሎማሲያዊ እና በሕዝባዊ እምቢተኝነት መስኮች በርካታ ስኬቶችን ያስመዘገበ ሲሆን የትግሉን ሂደት አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አስምሮበታል።
የኦሮሞ ህዝብ ተሳትፎ፣ ሚና እና ድጋፍ ለኦነሠ እድገት ትልቁ አስተዋፅዖ መሆኑን ተገነዝቦ እውቅና በመሰጠት፣ የኦነግ-ኦነሠ ማዕከላዊ ኮሚቴ፣ ተጨማሪ ጥሪም አቅርቧል። በአገር ውስጥም በውጭም ያለው የኦሮሞ ሕዝብ የትጥቅ ትግሉን ለማጠናከር በኦነግ-ኦነሠ ድርጅት ውስጥ ያለውን ተሳትፎ በእጥፍ በመጨመር፣ የጀመርነውን ትግል በሥነ ምግባር እና በፅናት በማጠናከር የኦነግ-ኦነሠ ግቦችን ለማሳካት ትግቶ እንዲሰራ የኦነግ-ኦነሠ ማዕከላዊ ኮሚቴ መመሪያ ሰጥቷል። በተጨማሪም፣ የኦሮሞ ምሁራን እና ባለሃብቶች ለዚህ ትግል ስኬት ወሳኝ ሚና ሲጫወቱ የነበረ መሆኑን በመገንዘብ ተሳትፏቸውን በእጅጉ በማሳደግ ታሪካዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ የኦነግ-ኦነሠ በተለይ ጥሪውን ያስተላልፋል።
በሌላ በኩል የኦነግ-ኦነሠ አሁን ያለውን የገዥው ፓርቲ ሁኔታ በዝርዝር በመተንተን፣ ቡድኑ የኦሮሞ ህዝብ እና የሌሎች ብሔሮች ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ ይፈታል የሚል ተስፋ እንደሌለው ጠቁሟል። የብልጽግና ፓርቲ መሪዎች ለሃገሪቱ ህዝቦች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ የገቡትን ቃል ከማጠፍ አልፈው ሀገሪቱን የጦር አውድማ አድርገዋታል። የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን እያሻሻሉ ሳይሆን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያባባሱት ይገኛሉ። ብልፅግና ኃይልን በመጠቀም ሰላማዊ ጥያቄዎችን ለማፈን ቢሞክርም የፖለቲካ ቀውሱን በኃይል መፍታት ካለመቻሉም በላይ ሀገሪቱን ወደ ለየለትና ማለቂያ ወደሌለው ጦርነት ከቷታል። እንደ የመደራጀት መብት፣ የመንቀሳቀስ መብት፣ ህዝባዊ ስብሰባ የማድረግ መብት፣ ማንኛውንም ድርጅት የመደገፍ ወይም የመቃወም እንዲሁም የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ያሉና መሰል መሰረታዊ ሰብአዊ መብቶችን ሁሉ ማፈኑን ቀጥሏል። የህግ የበላይነትን ለማስከበር በሚል ስም በህዝቡ ላይ ጦርነት እያወጀ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል። በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ሕግ በሌለበት ሐገር እና አመራሩ በሕዝብ ባልተመረጠበት ሐገር፣ የበላይነቱ የሚረጋገጥ ሕግ የለም።
በመሆኑም፣ ማዕከላዊ ኮሚቴው፣ ጠላት “ማስተዳደርም መተዳደርም በቀበሌ ደረጃ ነው” የሚል መፈክር ይዞ በህዝባችን ላይ አዲስ የእስር ቤት መዋቅር ለመመስረት ያቀደውን በመተንተን ተገቢውን እርምጃ አጠናክሮ እንደሚወስድ አቅጣጫ አስቀምጧል። የህዝቡን የፀጥታ፣ የፖለቲካ፣ የፍትህ፣ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ችግሮችን ለመፍታት ያለመ አንገብጋቢና ጊዜ የማይሰጡ ጥያቄዎችን በመለየት የመፍትሄ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል። ትኩረት ከተሰጣቸው እና በስፋት ከተወያየባቸው ጉዳዮች አንዱ፣ ብልፅግና በህዝባችን ውስጥ ሽብር ለመፍጠር ብሎ በህዝባችን ላይ እያደረገ ያለው አሰቃቂ የአንገት መቅላት ጉዳይ ነው። የኦነግ-ኦነሠ ማዕከላዊ ኮሚቴ ይህንን አንገብጋቢ ጉዳይ ተወያይቶበት እንዴት መስተናገድ እንዳለበት አቅጣጫዎችን አስቀምጦ ለተግባራዊነቱ ለኦነግ-ኦነሠ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ መርቷል።
በአሁኑ ወቅት የኦሮሞን ህዝብ አንድነት የመከፋፈል ሴራ እየተሸረበ ይገኛል። እናም ኦሮሞ ከነፃነቱ ትግል እንዲያፈገፍግ ለማድረግ ሰርጎ-ገቦችን ወደ ኦሮሞ የነፃነት ትግል ካምፕ ውስጥ የማስገባት ሲጎነጎን የቆየው ሴራ በነፃነት ሠራዊቱ ጥንቃቄ የተሞላበት እርምጃ ከሽፏል። የኢምፓየሪቱ ቀዳሚ ምርኮኞችም ሆኑ፣ አሁን እጅ የሰጡት ምርኮኞች፣ የበፊቶቹም ሆኑ የአሁኑ ሰርጎ-ገቦች፣ ኦሮሞ ነን እያሉ የኦሮሞን ህዝብ በመንደር፣ በክፍለ-ሀገር እና በሃይማኖት ለመከፋፈል የሞከሩት አንዳቸውም ኦነግንም ሆነ ኦነሠን እንደማይወክሉ፣ ለሰፊው የኦሮሞ ህዝብ ጥቅም ያልቆሙ፣ የዚህን ታላቅ ህዝብ አላማ ያላነገቡ፣ ርካሸ የግል ፍላጎታቸውን እና ጥቅማቸውን ብቻ የሚወክሉ መሆኑን የኦነግ-አነሠ ማዕከላዊ ኮሚቴ ያስገነዝባል።
ወደ ጠላት ካምፕ የገቡት እነዚህ ሰርጎ-ገቦች ለሌላ ጦርነት እየተዘጋጁ መሆናቸውን፣ DDR ለማካሄድ በሚል ቁጥራቸውን ከፍ አድርገው ሕዝቦችን ለመውጋት የሚያስችላቸውን ዶላር ከፈረንጆች ሊለምኑበት እየሰሩ መሆኑን የመረጃ ምንጮቻችን አረጋግጠዋል። በሥርዓቱ ታጥቀው በኦሮሞ ህዝብ ላይ ወንጀሎችን ሲፈፅሙ የነበሩትን ሰርጎ-ገቦች አሁን ደግሞ ትጥቅ እናስፈታለን በሚል ድራማ ፈረንጆችን እየለመኑ መሆኑ ተረጋግጧል። ሌብነት እና ልመናን ሥራው ያደረገ ስራዐት፣ ሥነ ምግባር የሌለው አገዛዝ መሆኑን ያሳያል። ሃቁ ግን እንደነዚህ ያሉ ወንጀለኞች የትግል ካምፑን ለቀው ሲወጡ የትግሉን ሜዳ ያጠራል፤ የህዝብን ትግልም ያጠናክራል! እየተሰራ ያለውን ድራማም ህዝባችን ነቅቶ እየቀለደባቸው ይገኛል።
እንደ ድርጅት ኦነግ-ኦነሠ በጨቋኙ አገዛዝ ላይ እንጂ በየትኛውም ብሔር ወይም ሃይማኖት ላይ አንዳችም ተቃውሞ ወይም ጥያቄ ኖሮት አያውቅም። ይህ ሊሆንም አይችልም። በሀገሪቱ ያሉ ብሔሮች የኢትዮጵያን ኢምፓየር መንግስታት ያረጀና የከፋፍለህ ግዛ ባህልን በመረዳት፣ በኦነግ-ኦነሠ እና በኦሮሞ ህዝብ ላይ እየተካሄደ ያለውን መርዘኛ ፕሮፓጋንዳ በሕዝቦችን ላይ የተጋረጠ የከፋፍለህ ግዛ ያረጀ ስልት አካል መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም። በኦሮሞ ህዝብና በሌሎች ብሔሮች መካከል ከበፊቱ የበለጠ ጠንካራ የወንድማማችነት ግንኙነት እንዲፈጠር እንጠይቃለን። አገዛዙ በኦሮሞ እና በሌሎች ብሔሮች መካከል የጎንዮሽ ግጭትን ህዝባችን ዉስጥ የማስፋፋት ዘዴን ቢጠቀምም፣ ይህን እኩይ ድርጊት አክሽፈን ትግላችንም የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ብቻ ላይ ትኩረት አድርገን ወደፊት ለመራመድ በቁርጠኝነት የተነሳን መሆኑና ማስታወስ እንወዳለን።
በኦሮሚያ ውስጥ በተለይ በኦሮሞ ህዝብ ላይ እየተካሄደ ያለው እስራት፣ ማሰቃየት፣ ዘረፋ፣ ማፈናቀል እና ግድያ፤ እንዲሁም በህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው ጥፋት እንዲቆም፣ ህዝባችን እየደረሰበት ያለው ከበባ እንዲነሳለት፣ በኦሮሚያ የቀጠለው ጦርነት እንደ ኦሮሞ በህይወት የመኖር መብታችንን እየነፈገ ያለ በመሆኑ ከዚህ ውርደት ለመውጣት በትጥቅ ትግል ከመፋለም ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌለ እጠቁማለን። በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ለምሳሌ በሰላሌ (ሰሜን ሸገር) የኢንተርኔት ግንኙነት ከተቋረጠ በኋላ አገዛዙ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈፀመ በመሆኑ በአንድነት እንድንፋለም አጥብቀን እናበረታታለን።
በሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች ከቀጠለው ጦርነት በተጨማሪ እንደ ሱዳን፣ ሶማሊያ እና ኤርትራ ካሉ ጎረቤት ሀገራት ጋር ያለው የጸጥታ ሁኔታ በሰላማዊ መንገድ ካልተፈታ የሀገሪቱም ሆነ የህዝቦቿ ደህንነት የባሰ ከባድ አደጋ ውስጥ ይወድቃል። ብልጽግና ህዝቡን በዚህ ጦርነት ለመማገድ ብሎ እድሜያቸው ለአቅመ አዳም ያልደረሱ ህፃናትን ጭምር ወደ ወታደራዊ ማሰልጠኛዎች እያጋዘ ይገኛል። ወጣቶች እንዳይማሩ የትምህርት ስርዓቱን አበላሽቶ፣ የዩኒቨርሲቲዎችን በመዝጋት፣ እንዲሁም ዜጎች ሥራ እንዳያገኙ በማድረግ ውትድርናን ብቸኛ የሥራ ዘርፍ አድርጎ በማቅረብ ወደ ማሠልጠኛዎች እያጋዘ በእሳት ለመማገድ በዝግጅት ላይ ይገኛል። ህዝባችን ይህንን የአገዛዙን እኩይ ተግባር በአግባቡ ተረድቶ መቃወም እንደሚገባው እንጠቁማለን።
በጠቅላላው ኦነግ-ኦነሠ፣ ከላይ የተዘረዘሩትን ችግሮች እንዴት መፈታት እንዳለባቸው አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ለመስራት የማያወላውል ቁርጠኝነት እና አቋም አለው። በሁሉም መልኩ ለትግላችን አላማ በቁርጠኝነት ለመስራት ወስነን ቃላችንን በማደስ ወደ ሥራ የገባን ሲሆን፤ አገዛዙ በሚረዳው ቋንቋ አጥብቀን ለማነጋገር ዝግጁ መሆናችንን እናረጋግጣለን። ስለሆነም የሰብአዊ መብቶች መከበር ማነቆ የሆነውን፣ እንዲሁም የህዝቡ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ምንጭ የሆነውን እንቅፋት አስወግዶ፣ የኦሮሞ ህዝብ የራሱን እድል በራሱ እንዲወስን ለማስቻል ያለውን ጠንካራ ቁርጠኝነት ያረጋግጣል። ከህዝቦች የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት በተቃራኒ ከማይቆሙ የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ሀይሎች ጋር ትግላችንን እናስተባብራለን!
ድል ለኦሮሞና ጭቁን ህዝቦች!
የኦነግ-ኦነሠ ከፍተኛ ዕዝ
ታህሳስ 07, 2024

