Site icon Qeerroo Bilisummaa Oromoo

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአብይ አገዛዝ የተፈፀሙት በደሎች፣ ስልታዊ በደሎች መሆናቸውን አረጋገጠ (ኦነግ-ኦነሠ መግለጫ)

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ የሰብአዊ መብት ጥሰት ተግባራትን አስመልክቶ ዓመታዊ ሪፖርት አስነብቧል። ሪፖርቱ ባለፉት ሰባት አመታት የህዝባችንን የሰቆቃ ህይወት፡ ማለትም፣ ስልታዊ ሽብር፣ በአገዛዙ የተቀነባበረ የጭካኔ ተግባር እና ስር የሰደደ ተጠያቂነት አልባ የጥፋት ሥራዎቹን በድጋሚ ያረጋግጠ ሆኗል።

ሪፖርት ከመዘገባቸው ጥቂቶቹ;

 ሰላማዊ ሰዎችን ያለአንዳች ፍርድ መግደል:- በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፣ በርካታ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ከበባ ተድርጎ ከህግ አግባብ ውጪ ግድያ ተፈፅሞባቸዋል።

 በሃይማኖት መሪዎች፣ በተቃዋሚ አመራሮች እና ባልታጠቁ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ያነጣጠረ ግድያ ተፈጽሟል።

 አገዛዙ፣ የትምህርት ቤት መምህራንን እና ነዋሪዎችን የገደለ፣ መሰረተ ልማቶችን ያወደመ እና ሆን ተብሎ ተዋጊ ባልሆኑ ዜጎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃትን ጨምሮ በሲቪል መሠረተ ልማት ላይ ያነጣጠረና ያለልዩነት በመደዳ የተፈፀመ የሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቃት አድርሷል።

 ስልታዊ የማሰቃያ እስሮች፥ በእስር ቤት ውስጥ በኤሌክትርክ ገመዶች መግረፍን፣ በርበሬ በተሞላ ከረጢት ውስጥ አስገብቶ በማፈን ማሰቃየትን፣ ምግብና ውሃ መከልከል እና ከቤተሰብ፣ ጠበቃ፣ ዘመድ እይታ አርቆ ለረጅም ጊዜ በማይታወቁ ቦታዎች ማሰርን ጨምሮ ስልታዊ የሆኑ የእስር ማሰቃያዎች ተፈጽመዋል።

 በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎች ያለ ክስ እና ፍርድ ቤት ትዕዛዝ አብዛኛውን ጊዜ በማይታወቁ ቦታዎች በጅምላ ታስረዋል።

 አስገድዶ መሰወር፡ የመብት ተሟጋቾች (አክቲቪስቶች)፣ ጋዜጠኞች እና የማህበረሰብ መሪዎች ታፍነው ወይም ተገድደው ተሰውረዋል፣ ያሉበት ቦታም ከቤተሰቦቻቸው ተደብቋል።

 የፕሬስ ነፃነት አፈና፦ በአገዛዙ ላይ ትችት የሚሰነዝሩ ጋዜጠኞችን፣ አርቲስቶችን እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን በማዋከብ፣ በማሰር እና በግዳጅ ከሀገር እንዲሰደዱ ማድረግ ቀጥሏል።

 መሰረታዊ የሀሳብ ነፃነቶች ክልከላ፦ ኢንተርኔት መዘጋትን፣ ሰላማዊ ስብሰባዎችን መከልከል እና በመንግስት የሚፈጸሙ ግፍቾን ለማድበስበስ ተብሎ ገለልተኛ ሪፖርት ማቅረብን ጨምሮ መሰረታዊ ነፃነቶችን ማገድ።

 ሰብአዊ እርዳታን እንደ ውግያ መሳሪያ መጠቀም ወይም ኢላማ ማድረግ ፦ ሆንተብሎ የህክምና ተቋማትን ኢላማ ማድረግ፣ የጤና ባለሙያዎችን ማዋከብ እና ማጥቃት እንዲሁም ግጭት የተከሰተባቸው አካባቢዎች እፎይታ እንዳይኖራቸው የመከልከል ተግባራት በኦሮሚያ እና በሌሎች አከባቢዎች ያለውን ሰብአዊ ቀውስ አባብሷል።

የሚሉ ይገኙበታል ።

በቀረበው ሪፖርት ውስጥ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (OLA) ስም በጥቂት ቦታዎች የተጠቀሰበትሆኔታን በተመለከተ፦

(ሀ) በሮይተርስ እና በዋሽንግተን ፖስት የተደረጉትን ጨምሮ ተዓማኒነት ያላቸው ገለልተኛ ምርመራዎች እንደሚያሳዩት የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (ኦነሠ) የተከሰሰባቸው ክሶች፤ አንድም በቀጥታ በአገዛዙ የተፈጸሙ አሊያም አገዛዙ የኛን የነጻነት እንቅስቃሴ ለማጠልሸት ሆን ብሎ አደራጅቶ በሚዘወረው የራሱ ሸኔ የተፈጸሙ ወንጀሎች መሆናቸውን።

(ለ) የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (ኦነሠ) በተደጋጋሚ ሲጠይቅ እንደቆየው ፡ በሁሉም ውንጀላዎች ላይ ገለልተኛና፣ በአለም ዓቀፍ ደረጃ ለሚደረጉ ምርመራዎች ሙሉ ትብብር ለማድረግ ፅኑ ፍላጎት ያለው መሆኑን ይገልጻል። በኣንጻሩ ኣገዛዙ ገለልተኛ ምርመራም ሆነ ዘገባ እየከለከለ ቀጥሏል።

ከእነዚህ ግኝቶች አንፃር፣ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (ኦነሠ)፣ የዩናይትድ ስቴትስ መንግስት ሁሉንም በሁለትዮሽ እና ባለብዙ ወገን ግንኙነት ማእቀፍ የሚደረጉ ድጋፎችን፣ በዓለም ዓቀፉ የገንዘብ ተቋም እና ዓለም ባንክ አማካይነት የሚደረጉትን ጨምሮ፣ ለአገዛዙ የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲያቋርጥ እና ሀገሪቱን ወደ ሰላም፣ ዲሞክራሲ እና ተጠያቂነት የሰፈነበት ሂደት ለማሻገር አማራጭ ሆነው እየወጡ ካሉት ተቃዋሚዎች ጋር በመርህ ላይ የተመሰረተ ውይይት እንዲጀምር ጥሪ እናቀርባለን።

የኦነግ-ኦነሠ ከፍተኛ ዕዝ

ኦገስት 13፣ 2025

Exit mobile version