Site icon Qeerroo Bilisummaa Oromoo

ኦነግ እና ኦፌኮ ከገዥው ቡድን ጋር በሚያደረጉት ውይይት/ንግግር ዙሪያ ሁለት ዋና ዋና ትርክቶች (የኦነግ-ኦነሠ ጋዜጣዊ መግለጫ)

ሰሞኑን ባወጣነው መግለጫ፣ የአብይ አገዛዝ በኦሮሚያ ውስጥ በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት – ኦነሠ ላይ በወሰዳቸው ተከታታይ እርምጃዎች ሳይሳካለት በመቅረቱ፣ በዋነኛነት የኦሮሞ ፓርቲዎችን በመጠቀም የተጋረጠበትን የቅቡልነት ቀውሱን ለማቃለል ተስፋ የመቁረጥ እርምጃዎችን ለመውሰድ መወሰኑን መግለጻችን ይታወሳል። በኦነግ-ኦፌኮ እና በአብይ መንግስት መካከል የሚደረጉትን ንግግር (ድርድር) ተቀባይነት ያለው ለማድረግ በዋናነት በገዥው ቡድን ሁለት ተደጋጋሚ ትርክቶች ጎን ለጎን እየቀረቡ ይገኛሉ። (ሀ) ኦነሠ (OLA) እራሱ በታንዛኒያ ድርድር ላይ ተሳትፎ የነበረ በመሆኑ ይሄኛውንም ድርድር መሞከሩ የሚያስከትለው ጉዳት የለም የሚል አባባል እና (ለ) “የሰሜን ሀይሎች መንግስትን የመገዳደር ኃይላቸውን አጠናክረው እየመጡ በመሆኑ ኦሮሞው መንግስትን ለመታደግ አንድ መሆን አለበት’’ የሚል ናቸው።  

ሀ) በውይይት መሳተፍ ምንም ጉዳት የለውም የሚለው ሲፈተሽ

  1. በኦነሠ (OLA) እና ፊንፊኔ ባሉ የኦሮሞ ፓርቲዎች መካከል የውሸት አቻነትን መፈብረክ  

ኦነሠ በታንዛኒያ ከገዥው ቡድን ጋር በመገናኘት ድርድር እንዳደረገው ሁሉ ፊንፊኔ ውስጥም መነጋገር ምንም ችግር የለበትም የሚለው አባባል በመሠረቱ ስህተት ነው። ኦነሠ ወደ ድርድር የገባው ኣገዛዙ የሚረዳውን ብቸኛውን ተገዳዳሪ የሃይል ሚዛን ይዞ ነው። የራሱን ተዋጊ ሃይሎች ያሉት፣ የኦሮሚያን ሃብት ለመበዝበዝ የተሰማራን የአገዛዙን አቅም በማዳከም፣ አገዛዙ የተመካበትን ከፍተኛ የታክስ እና የግብር ገቢ ቁጥጥር ያሳጣ አቋም ላይ ሆኖ ነው። እነዚህ ምክንያቶች፣ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ከፍተኛ የመደራደር ጥቅም እንዲያገኝ በማድረግ በአስተማማኝ መሰረት ላይ ሆኖ እንዲደራደር እና በውይይቱም የኦሮሞን ህዝብ ጥቅም ጠበቆ ለመደራደር አስችሎታል።  

በተቃራኒው በፊንፊኔ የሚገኙ የኦሮሞ ፖለቲካ ፓርቲዎች ስልታዊ በሆነ መንገድ ከፖለትካ እንቅስቃሴ ተገድበው፣ የፖለቲካ አቅማቸውን እንዳያጠናክሩ በመታገዳቸው አገዛዙን ለመገዳደር የሚያስችል ትርጉም ያለው ጉልበት እንዳይኖራቸው ተደርገዋል። የመደራደር አቅም ሳይጎለብት የሚደረገው ማንኛውም ድርድር በባህሪው ያልተመጣጠነና፣ ሂደቱም በጥቂቱም ቢሆን ለአብይ አህመድ ቅቡልነት ማስገኛ እና በኦሮሚያ ውስጥ እየሞተ ያለውን የአገዛዙን ገፅታ እንደገና ለመገንባት የተነደፈ ትወና ስለመሆኑ ከልምድ የምናውቀው ነገር ነው።  

በታንዛኒያ በኦነሠ እና በአገዛዙ መካከል የተደረጉት ድርድሮች ዓለም አቀፍ የድርድር መስፈርቶችን ያሟሉና በገለልተኛ ሶስተኛ ሀገር፣ በገለልተኛ ሸምጋዮች አማካይነት ሲሆን ተደራዳሪ ልዑካን ለህዝባችን ጥቅም በነፃነት መሟገት በሚችሉበት ካባቢያዊ ሆኔታ ውስጥ ነበር። በአንፃሩ በፊንፊኔ በኦነግ-ኦፌኮ እና በአገዛዙ መካከል ሊካሄድ የታቀደው ውይይት በሶስተኛ ወገን ሸምጋይነት የሚደረግ ሳይሆን በአገዛዙ ቀጥተኛ ቁጥጥር ሥር የሚደረግ ነው። ታሪክ ደጋግሞ የሚመሰክረው የመደራደር አቅም ሳይጎለብት በጨቋኝ አገዛዝ ቁጥጥርና የገንዘብ ድጋፍ ሥር ከሚካሄደው ድርድር ሁልጊዜ ተጠቃሚው ሥልጣን ላይ ያለው ቡድን ሲሆን በውጤት ደረጃ አቻ ወዳልሆነ ትብብር የሚያመራ ወይም በስልጣን ላይ ያለውን አገዛዝ ለመጥቀም ብቻ የሚያገለግል ይሆናል። የአብይ አህመድ አሁን ያቀረበው የውይይት ግብዣ ሀቀኛ ሳይሆን ተቃዋሚዎችን ወደ ጉያው ሥር የመጠቅለል ስልት ነው። የዚህ ዓይነቱ ድርድር ውጤት ለገዥው ቡድን ብቻ እንዲውል ተደርጎ አስቀድሞ የተወሰነ ነው። በዚህ ውይይት አብይ አህመድ እና ሽብርተኛው አገዛዙ የምያቀርቧቸውን የመደራደሪያ ሃሳቦች ኦነግ እና ኦፌኮ ቢቀበሉም ባይቀበሉም የውጤቱ ተጠቃሚ አብይ አህመድ እና ሽብርተኛው አገዛዙ እንደሚሆኑ አስቀድሞ የተረጋገጠ ጉዳይ ነው። ኦነግ እና ኦፌኮ የአብይ አህመድን የድርድር ሃሳብ ከተቀበሉ፣ አነስተኛ የግል እና የፓርቲ ጥቅሞችን ብቻ ጠብቆላቸው ወደሚፈልገው መስመር ይጠቀልላቸውና ስልጣኑን ያጠናክራል ። የተቃዋሚ ኣመራሮቹ በመርሃቸው ጸንቶ የድርድር ሃሳቡን ውድቅ ቢያደርጉበትም የድርድር ሂደቱን በመጠቀም በኦሮሚያም ሆነ ከዚያም በላይ ራሱን ከኦሮሞ ጋር ሰላም ለመፍጠር ፈቃደኛ የሆነ መሪ በማስመሰል የሞተ ገጽታውን ይገነባበታል።

ባንጻሩ በሁለቱም ሁኔታዎች ተቃዋሚዎች ምንም አያተርፉም።

ለ) ‘’የኦሮሞ መንግስትን ለመጠበቅ የኦሮሞ አንድነት’’  

በተጨማሪም አገዛዙ ከኦሮሞ ፓርቲዎች ጋር ብቻ ንግግር እያደረገ ያለው  “የሰሜን ኃይሎች ጥረቶቻቸውን አጠናክረው መንግስት ላይ ስጋት እየፈጠሩ በመሆኑ ኦሮሞው ተባብሮ ‘መንግስቱን’ ሊጠብቀው ይገባል” እያለ ነው። እንደገና፣ ከዚህ አባባል በስተጀርባ ያሉት ግምቶች እና አጠቃላይ አንድምታዎቻቸው ቀጥሎ በቀረቡት ምክንያቶች የተሳሳቱ እና መሰረታዊ ችግር ያለባቸው ናቸው።

አንደኛ፣ አብይ አህመድ ኦሮሞው መንግስትን ለመጠበቅ አንድ መሆን አለበት ሲል የተቃዋሚ መሪዎች አሁን ያለው አገዛዝ ‘’የኦሮሞ መንግስት ነው’’ የሚለውን አባባል በተዘዋዋሪ እንዲቀበሉ ለማድረግ እየሞከረ ነው። በመላው ኦሮሚያ “የኦሮሞ መንግስት ነኝ” እያለ  ቅቡልነት ለማግኘት ተደጋጋሚ ጥረቶችን ቢያደርግም ትክክለኛ ቀለሙን ሊደብቅ አልቻለም። ህዝባችን በስልጣን ላይ ያለው ገዥ ቡድን ከሱ ያገኘው ምንም አይነት ስልጣን እንደሌለው ብቻ ሳይሆን የህዝባችንን የለውጥ ፍላጎትና ሃሳብ በጠለፉ እና በከዱ ግለሰቦች እንደሚመራ፣ ባለፉት ስርዓቶች ጭቆናን የማስቻል አስከፊ ታሪክ ያላቸው እና በአመራርነታቸው ከፍተኛ የራዕይ ጉድለት እና የብቃት ማነስ ችግር ያለባቸው ግለሰቦች መሆናቸውን ህዝባችን በሚገባ ይገነዝባል።

በዚህ ጊዜ ሊጠበቅ የሚገባ “የኦሮሞ ሥልጣን” እንደሌለ ለማንም ግልፅ ነው። ያለው በኦሮሞ ህዝብ ስም የሚነግድ የብጥብጥ፣ የሽብር እና ጭቆና  አፋኝ ስርዓት ነው። ይህ ስርአት በምንም መመዘኛ መበተን እንጂ መጠበቅ ያለበት ኣይደለም። የሚገርመው ነገር ደግሞ ይህ እውነታ በህዝብ ዘንድ የማይካድ ሆኖ ሳለ፣ አብይ ግን አሁንም ይህንን የከሰረ ሀሳቡን የተቃዋሚ መሪዎችን በግድ ለመጋት መሞከሩ ነው።

በሁለተኛ፣ ይህ አባባል የኦሮሞን ህዝባዊ ንቅናቄ የሚሳደብ ነውር ነው። አብይ አህመድ፣ ኦሮሞው ተባብሮ ስልጣኑን “ከሰሜኑ ሃይሎች” ይጠብቅ ሲል፣ የኦሮሞ ፖለቲካ በሰሜኑ ጥላቻ እና ጠላትነት ላይ የተመሠረተ ነው ማለቱ ነው። ይህ ትርክት ለፍትህ ውድ ህይዎታቸውን ለገበሩ ጓዶቻችን ኣስነዋሪ ስድብ ብቻ ሳይሆን በህጋዊ እና ህዝባዊ ጥያቄዎች ላይ ለተመሰረተው ታሪካዊው የኦሮሞ ትግል እጅግ ጎጂም ነው። የኦሮሞን ፍትሃዊ እንቅስቃሴ ትክክለኛ ባህሪ የሚያዛባ እና ለረዥም ጊዜ የቆዩ አሉታዊ አመለካከቶች እንዲቀጥሉ የሚያደርግ ነው።

የኦሮሞ ትግል በጥላቻ የሚመራ ሳይሆን፤ ለፍትህ፣ ለእኩልነት እና የራስን እድል በራስ ለመወሰን የሚደረግ የመብት ትግል ነው። መርሆቹ እና አላማዎቹ ግልፅ እና መሰረቱም የህዝባችን መሰረታዊ መብቶች እና ብሄራዊ ክብርን ማስከበር እንጂ የማንም ጠላትነት አይደለም። የአብይ “የኦሮሞ አንድነት” በትክክል ሲገለፅ የኦሮሞን እንቅስቃሴ በጎሳ ከፋፍሎ የሚያሳይ፣ የትግላችንን ተቀባይነትም ጥላሸት ለመቀባት ሆን ተብሎ የሚደረግ የማዛባት ተግባር ነው። የኦሮሞ ህዝብ ትግል መሰረቱ ሁለንተናዊ የፍትህ እና የነጻነት እሴቶች እንጂ የብሄር ጥላቻ ጠባብ ፖለቲካ አይደለም።

ሦስተኛ፣ ከአብይ አህመድ ጋር ‘’አንድነት መፍጠር’’ የሚለው አስተሳሰብ ፡  በየሳምንቱ ኣጋርን በመለወጥ፣ ከኋላ በመውጋት፣ በጠላትነት በመፈረጅ እና በመካድ እና በመሳሰሉ እርካቦች መንበር ይጸናል ከሚል ግለሰብ ጋር መሆኑ ነገሩን ለማሰብም ሆነ ለመረዳት አዳጋች ያደርገዋል። ብዙ ድጋፍ በነበረበት የስልጣን ጫጉላው ወቅት የአማራን ልሂቃን ድጋፍ በመታበይ በኦሮሞ ላይ ጦርነት ከፈተ። በመሆኑም፣ ኦነሠ፣ ኦፌኮን፣ ኦነግን እና በራሱ ፓርቲ ውስጥ ያሉ ወሳኝ ግለሰቦችን ኢላማ በማድርግ ደም ኣፈሰሰ ። በኋላ ላይ ይሄው የድጋፍ መሰረት፣ ከውጭ ኃይል ጋር ሆኖ፣ በትግራይ እናቶች ላይም ጥቅም ላይ እንዲውል አደረገ። ቀጥሎም የለመደውን ክህድት በመፈጸም ሰይፉን ወደ አማራው አዞረ።

አሁን ደግሞ፣ በስልጣን ላይ የሙጥኝ ለማለት ሌላ የፖለቲካ ህይወት ለመዝራት ወደ ኦሮሞ ፓርቲዎች ዞሯል። ልክ ከሁለት ዓመት በፊት ለአማራ ጥቅም አጥብቆ የሚቆም መስሎ እራሱን ሲያቀርብ የነበረው አብይ አህመድ አሁን ደግሞ የኦሮሞን አንድነት “በሰሜኖቹ” ላይ አደራጃለሁ እያለ ነው። ለመሆኑ ባለፉት ስድስት ዓመታት በነበሩት ‘የለውጥ’ ጊዜዎች፣ አብይ አህመድ በመጨረሻ ላይ ያልከዳው ጥምረት ወይም ሽርክና ነበር ?

አገዛዙ በኦሮሚያ ውስጥ ለኦሮሞ አንድነት ዋነኛው እንቅፋት መሆኑን በተደጋጋሚ አስመስክሯል። ከአብይ አህመድ ጋር ሆኖ የሚገኝ አንድነት የለም። የተሰረቀብህን ከሌባው ጋር በመፈለግ ማግኘት አትችልም።

አራተኛ፣ አብይ አህመድ ”የኦሮሞን አንድነት በሰሜኑ ህዝብ ላይ” በሚፈልግበት በኣሁኑ ወቅት በህዝባችን ላይ የማይታመን ሞት፣ ውድመት እና ስቃይ ያለማቋረጥ እያስቀጠለ ቀጥሏል።  የሀገር ሽማግሌዎች እና የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች በፊንፊኔ በሚገኙ ሆቴሎች እና ያጌጡ አዳራሾች ስብሰባ በተቀመጡበት ወቅት አገዛዙ እስካሁን ታይቶ የማይታወቅ ጥቃት በህዝባችን ላይ እየፈፀመ ይገኛል።

ስለዚህ ከአብይ አህመድ ጋር ለኦሮሞ አንድነት እንሰራለን ማለት:-  

  1. አብይ በርግጥም የኦሮሞን መንግስት ይመራል ብሎ ማረጋገጫ እንደ መስጠት ነው።  
  2. የኦሮሞ ፖለቲካ የሚመራው በጥላቻ እንጂ በተቆጠሩ ህዝባዊ አጀንዳዎች አለመሆኑን እንደ መቀበል ነው።  
  3. አብይ አህመድን እንደ ታማኝ አጋር መቁጠር እና
  4. አሁን በኦሮሚያ እየፈፀመ ያለውን ተግባር ተቀባይነት እንዳለው አድርጎ እንደ ማፅደቅ ይቆጠራል። 

ምርጫው ግልጽና ጥርት ያለ ነው።

የኦነግ-ኦነሠ ከፍተኛ ዕዝ

የካቲት 20 ቀን 2025

Exit mobile version