ሀ. ይህ “የሰላም ሂደት” በኣገዛዙ የተቀናበረ ከቁምነገር ሊወሰድ እንደማይችል መሆኑን በድጋሚ እንገልፃለን
የኦሮሞ ፖለቲካ ፓርቲዎች አጋጣሚውን ለመጠቀም ቢሞክሩም፣ በቅርቡ የተካሄደው የኦነግ እና ኦፌኮ ኮንፈረንስ እና ከአገዛዙ ጋር የተደረገው ውይይት በመሰረቱ የአብይ አህመድ ፕሮጀክት ነው። በአገዛዙ አነሳሽነት እና የገንዘብ ድጋፍ የተደረገ ነው። አገዛዙ የውይይቱን አድማስ እና ሂደቱን ባስቀመጣቸው ግቦች ላይ በመመስረት የሚቀጥልበትን ሁኔታ ይቆጣጠራል እና ይወስናል። በኮንፈረንሱ ላይ የተሳተፉት ሁለቱ ፓርቲዎች እና የሀገር ሽማግሌዎች ብቻ እንደሆኑ ዘገባዎች ቢጠቁሙም፣ ከ 11 ያላነሱ የኢትዮጵያ ብሄራዊ መከላከያ ሰራዊት እና የመረጃ አመራር አካላት ተገኝተዋል። አገዛዙ ስለ ኦነሠ (OLA) በሽማግሌዎቹ ሲጠየቅ፣ በደቡብ አፍሪካ ከኦነሠ (OLA) ጋር በድብቅ እየተነጋገረ እንደሆነ ለሽማግሌዎች እና የተቃዋሚ መሪዎች በመዋሸት ሂደቱን አስጀመረ።
ገና ከጅምሩ በሥፍራው የተገኙ የሀገር ሽማግሌዎች በአገዛዙ ሀብት የተመረጡ ናቸው። የትኛውም የኦሮሞ ማህበረሰብ ህዝባችንን እንዲወክሉ ስልጣን አልሰጣቸውም። በኦሮሞ ባህል ውስጥ የተከበረው የጃርሱማ (የሽማግሌነት) ተቋም ለርካሽ የፖለቲካ ቁማር እየተበዘበዘ መቀጠሉን ያሳየ አጋጣሚም ሆኖ ተመዝግቧል። ይህ ግርግር የተከበረውን የሀገር ሽማግሌነት ተቋምን ከማዋረድ ባለፈ የተቃዋሚ መሪዎችን እራሳቸውንም አዋርዷል። በአንድ በኩል ተቃዋሚዎች የሽግግር መንግስት መመስረትን ጨምሮ ጥያቄዎችን እንዲያነሱ እየተፈቀደላቸው፣ በሌላ በኩል የአገዛዙ የሚዲያ አካላት እንዲህ አይነት ጥያቄዎችን ማቅረባቸው ቅዥት በማለት ተሳልቀዋል፣ ተሰማርተዋል።
ከጉባኤው በኋላ የሀገር ሽማግሌዎች ለሁለቱም ፓርቲዎች “ሁነኛ ኃላፊነት” የሰጧቸው መሆኑ ታውቋል። በዘፈቀደ የተመረጡ የሀገር ሽማግሌዎች ቡድን፣ ቢሯቸው ክፍት እንዲሆን እንኳን ያልተፈቀደላቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎችን – ጦርነት የማስቆም፣ ሰላም የማስፈን እና መንግስት የመመስረት ከፍተኛ ኃላፊነት ሊሰጥ የሚችለው በአብይ አህመድ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ነው። የእንደዚህ አይነቱን ኃላፊነት ህጋዊ መሰረት፣ ቅቡልነት ወይም አዋጭነት፣ እና እንዴት ሊፈፀም እንደሚችል ጥያቄ ያነሳ ሰው የለም።
በተጨማሪም ከጉባዔው በኋላ የወጣው መግለጫ ኦነሠ (OLA) ወክሎ እንደመናገርና ሚናውንም የመወሰን ዳርዳርታ ታይቶበታል። በአሁኑ ጊዜ እውነታው ለራሱ ስለሚናገር ይህ ዋና ጉዳይ ባይሆንም ኦነሠ ራሱን የቻለ የፖለቲካ እና ወታደራዊ ተቋም፣ የራሱ አደራጃጀት እና ውክልና ያለው መሆኑን አጽንኦት መስጠት አስፈላጊ ነው። የትኛውም የፖለቲካ አካል ከነፃነት ሠራዊቱ አመራር ጋር ተገቢውን ድርድር ሳያደርግ ስለ ኦነሠ ኃላፊነት ሊወስድ ወይም ሚናውን ሊወስን አይችልም።
ለ. ከዚህ ፕሮጀክት ጋር ተያይዞ የአብይ አህመድ ዓላማዎች
1. ኦሮሚያን እንደገና መበዝበዝ
አብይ አህመድ ህዝባዊ መሰረት ስለሌለው እና በአንድ ወቅት ያገኘው ተዘዋዋሪ ድጋፎችንም በእያንዳንዱ የህብረተሰብ ክፍል ላይ ጦርነት በማወጅ በትኗል። በኦሮሚያ ያሉ ተቃዋሚዎች ስሜት ኮርኯሪ ጉዳዮችን እንዲያነሱ እና የሽግግር መንግስት ሊኖር እንደሚችል የሚጠቁሙ መግለጫዎችን እንዲያወጡ በመፍቀድ፣ አገዛዙ በኦሮሚያ ውስጥ የለውጥ ስሜት ለመፍጠር እና በፍጥነት እየተበላሸ የመጣውን ገጽታውን ለማደስ ያለመ ነው።
አገዛዙ ይህንን የተፈበረከ የተስፋ ማዕበል ተጠቅሞ የህዝቡን ድጋፍ ለመቀራመት የራሱን “የሰላም ኮንፈረንስ” በመላው ኦሮሚያ ለማዘጋጀቱ ጊዜ አላጠፋም። እነዚህ ጥረቶች የተነደፉት ተቃዋሚዎች በቅርቡ ካወጡት መግለጫ የመነጩትን ማንኛውንም ብሩህ ተስፋ ለመጠቀም ነው። አገዛዙ እነዚህን ጥረቶች ፍሬያማ አድርጎ ከተገነዘበ፣ በሚቀጥሉት ሳምንታት ውስጥ “የሽግግር” ወይም “የአንድነት’’ መንግስት በማስመሰል የካቢኔ ቦታዎችን ለተቃዋሚ መሪዎች ሊሰጥ ይችላል።
በአገዛዙ የተጀመሩ፣ በመንግስት የገንዘብ ድጋፍ እና የቁጥጥር ሥራ በሚደረግባቸው ውጥኖች ውስጥ መሳተፍ፣ የመካከለኛ እና የረጅም ጊዜ አንድምታዎችን እንደሚያስከትል ተቃዋሚዎች በጥልቀት እንዲገመግሙ እናሳስባለን። በተለይ የኦፌኮ አመራር ያሳየውን ጥንቃቄ የተሞላበት አካሄድ ብንገነዘብም፣ የአገዛዙ መሣሪያ እንዳይሆን የበለጠ ጥንቃቄ እንዲደረግ እናሳስባለን። እንዲህ አይነት ውይይት ህዝባችንን እየገደለ ያለውን አገዛዝ በህዝባችን ላይ ተጨማሪ የስቃይ ዘመን ከማራዘም በስተቀር ለህዝባችን ችግር ተጨባጭ እልባት ማስገኘት ያልቻለው “እየታገልን እንደራደራለን” ብሎ መግለጽ ብቻውን በቂ አይሆንም። ከአገዛዙ ጋር ቀጣይነት ያለው ግንኙነት ለሰፊው ትግል የሚያገለግል ወይም አገዛዙን የሚያዳክም መሆኑን በጥልቀት መገምገም አስፈላጊ ነው። እስካሁን ድረስ ሁሉም መረጃዎች የሚያሳዩት ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚጎላ ነው።
ህዝባችን በንቃት መከታተል አለበት። አገዛዙ እንደዚህ አይነት ትኩረት ማስቀየሪያ ስልቶችን ሲተገበር ይህ የመጀመሪያው አይደለም። አብይ አህመድ ከዚህ ቀደም በርካታ የሀሰት የፖለቲካ ትዕይንት ስራዎችን አቀነባብሯል። ከፊንፊኔ የሚነሳ እያንዳንዱ ፕሮጄክት በአገዛዙ ቁጥጥር ስር መሆኑን ኣለመዘንጋት ተገቢ ነው። የለውጥ ስሜት ለማንፀባረቅ ምንም ምክንያት የለም።
- አከራካሪ የድንብር እና ሌሎች ይጉዳዮችን በመጠቀም በአገሪቱ ህዝብ መካከል ኣጋርነት እንዳይኖር ማድረግ
ከተቃዋሚዎቹ ኮንፈረንስ በፊትም አገዛዙ እንደ ድሬዳዋ፣ መደ ወላቡ እና ሞያሌ ባሉ አወዛጋቢ ጉዳዮች ላይ ውጥረት መቀስቀስ መጀመሩ ይታወቃል። አሁን አገዛዙ እነዚህን ክፍፍሎች ለማጉላት የተቃዋሚውን ኮንፈረንስ መጠቀሚያ እያደረገ ነው። የአገዛዙ ስትራቴጂ የኦሮሚያን ድንበር እና ፊንፊኔን የመሳሰሉ ከፋፋይ ርዕሰ ጉዳዮችን በማስተጋባት በሀገሪቱ ህዝቦች መካከል አለመግባባት እንዲፈጠር ማድረግ ነው። ይህ በኦሮሞ ተቃዋሚዎች እና ሌሎች ማህበረሰቦች መካከል አገዛዙን የሚቃወም ጠንካራ ጥምረት እንዳይኖር ለመከላከል ያለመ ነው።
የኦሮሞ ህዝብ በእነዚህ በተጠቀሱ አከባቢዎች ላይ ትክክለኛ ስጋቶች ቢኖሩትም እነዚህ ጉዳዮች ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ባሳተፈ ድርድር መፈታት ያለባቸው ናቸው። አሁን ግን ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው በህዝባችን ላይ የእለት ተእለት ጥቃት የሚያደርሰውን አገዛዝ ማስወገድ ነው። በመላ ሀገሪቱ ላላችሁ ማህበረሰቦች፣ አብይ አህመድ የጎንዮሽ ውጥረቱን ለማቀጣጠል በሚያደርገው ሙከራ ትኩረታችሁን ከጨቋኝ አገዛዙ ለማዞር መሆኑን በመገንዝብ፣ ለእነዚህ ከፋፋይ ኣጀንዳዎች እድል እንዳትሰጡ እናሳስባለን። የሚዲያ ተቋማትም ትኩረታቹን አገዛዙ ላይ ብቻ እንዲሆን እንመክራለን። እነዚህ ጉዳዮች በጊዜያቸው በውይይት የሚፈቱ ይሆናሉ። አሁን ላይ የጋራ ትኩረታችን፣ ሁሉንም እየጨቆነ የሚገኘውን ስርዓት በመቃወም የጋራ ግንባር መፍጠር ላይ ማድረግ አለብን።
- በኦሮሞ ተቃዋሚዎች መካከል ክፍፍል መፍጠር
የአብይ አህመድ አንዱ አላማ በኦሮሚያ ተቃዋሚ ድርጅቶች መካከል ጥላቻን መዝራት ነው። የኛ የጋራ እንቅስቃሴ በክልሉ እያሽቆለቆለ ያለውን የአገዛዙን ቅቡልነት የመጨረሻ ሽንፈት እንደሚያስከትልበት አብይ አህመድ ተረድቷል። ይህንን እድል ልንሰጠው አይገባም። ነባራዊ ሁኔታዎችን እና እውነታዎችን በግልጽ መነጋገር አስፈላጊ ቢሆንም፣ ለሕዝባችን ስንል አንድነታችንን መጠበቅ አለብን። መከፋፈል እና መነጣጠልን በሚሻ አገዛዝ ፊት አንድነት ትልቁ መሳሪያችን ነው።
በመጨረሻም፣ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም እነዚህን ለውጦች በተመለከተ ነቅቶ መጠበቅ አለበት። ይህ በኦሮሚያ ውስጥ ያለው ሁኔታ አብይ አህመድ የጭቆና ንግሥናውን ለማስቀጠል በሚያደርገው የተራዘመ የጭካኔ ጨዋታው ውስጥ ሌላው ቁማር ነው። አለመግባባትን በመዝራት እና የተባበረ የተቃዋሚዎች እንቅስቃሴን በማዳከም እየተንገዳገደ ያለውን የአገዛዝ ዘመኑን ለማራዘም ያለመ ነው። አለም ይህንን ሴራ ተገንዝቦ ለፍትህ እና ለነጻነት የሚደረገውን የጋራ ትግል ለሚያበላሹ ተግባራት እውቅና ከመስጠት መቆጠብ አለበት።
የኦነግ-ኦነሠ ከፍተኛ ዕዝ
የካቲት 24 ቀን 2025 ዓ.ም

