በጾታ ላይ የተመሰረተ ጥቃት በማንኛውም ማህበረሰብ ውስጥ ካሉት እጅግ አስከፊ ወንጀሎች አንዱ ነው። በኦሮሚያ እና ከዚያም ባሻገር በመላ ሃገሪቱ በሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ የሚደርስ ማንኛውም የወሲብ ጥቃት በግልጽ መወገዝ ያለበት፣ በተናጥል እራሱን ችሎ መመርመር እና ክስ መመስረት ያለበት ከባድ የኢፍትሃዊነት መገለጫ ነው። የትም ቢከሰት እና የፈጸመው ማንኛውም ሰው ቢሆን ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም። በሲቪሎች፣ በተለይም በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን መካድ፣ ምክንያታዊ አድርጎ መሞገት ወይም ማሳነስም ተቀባይነት የለውም። በኦሮሚያ ውስጥ የተከሰቱት እነዚህ በደሎች ለረጅም ጊዜያት ተደብቀው የቆዩ ሲሆን፣ የችግሩ ተጠቂዎች ያሳለፉትን ስቃይ ለመመዝገብ እና ችግራቸውን ለዓለም አቀፍ ትኩረት ለማቅረብ የሚደረገውን ማንኛውንም እውነተኛ ጥረት በደስታ እንቀበላለን።
ሆኖም፣ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል «ማንም ሊያድነኝ አልመጣም» በሚል ርዕስ ያወጣው ሪፖርት፣ ለረጅም ጊዜ ትኩረት ለተነፈጉት ከባድ ጥቃቶች ትኩረት የሳበ ቢሆንም፣ በጥልቀት ሲመረመር ከፍተኛ ጉድለቶች ያሉትና ለተጎጂዎች ፍትሕን ከመፈለግ ይልቅ ሌላ ኣላማ ለማሳካት የኳተነ ሆኖ ተገኝቷል። ሪፖርቱ የጥናት ዘዴ ድክመት፣ መሠረታዊ የእውነታ ስሕተቶች እና በአንዲት የተወሰነች ትኩረት ውስብስብ የሆነውን ጦርነት በአደገኛ ሁኔታ ኣቅልሎ ያቀርባል። ከሁሉም በላይ ደግሞ፣ የታጠቁ ተዋናዮች የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊትን ተመስለው የሚፈበረኩበት፤ በሚገባ የተዘገበ ክስተት ሆኖ እያለ ይህንን ዞር ብሎ ያላየ ሲሆን፡ ይህ እውነታ በዋሽንግተን ፖስት፣ ሮይተርስ እና በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ጭምር በተናጥል የተረጋገጠ ነው። ይህ መሠረታዊ ጉዳይ ነው። ወንጀለኞችን በአስተማማኝ ሁኔታ መለየት በማይቻልበት ጊዜ ተጠያቂነት ማስፈን በፍጹም የማይቻል ስለሚሆን፤ ይህ ክፍተት በሪፖርቱ ላይ መኖሩ ግን ጉዳት የደረስባቸውን የእህቶቻችንን ስቃይ አያሳንስም። የሪፖርቱ ዋና ዋና ክፍተቶች እንደሚከተለው ቀርቧል።
1) ዋነኛው ኃጢአት፡ ወንጀለኞቹን መለየት አለመቻል እና «የሐሰት ኦነሠ» ኃይሎችን ፈጽሞ እንደሌሉ መቁጠር
የዚህ ሪፖርት አስከፊ ውድቀት ወንጀለኞቹን በትክክል መለየት አለመቻሉ ነው። በገጽ 15 ላይ፣ አምነስቲ የሚከተለውን በግልጽ አምኖ ይቀበላል፡ ሪፖርቱ «በታተመበት ጊዜ ማንነታቸውን (የወንጀለኞቹን) ማረጋገጥ አልቻልንም።» በእንደዚህ ዓይነት ምርመራ፣ ወንጀለኛውን መለየት ካልቻልክ፣ ወንጀል መርምረህ መደምደምያ ላይ መድረስ ይቅርና፤ ክስ መጀመርም አትችልም። ወንጀለኛውን ሳትለይ ማንን ትከሳለህ? የጦር ወንጀሎችን ለመበየን ለሚፈልግ የሰብአዊ መብቶች ሪፖርት፣ ይህ የእምነቱ ማረጋገጫ ብቻ ሪፖርትቱን ይፋ ከማድረግ መቆጠብ የሚያስችለው መሆን ነበረበት።
በተጨማሪ የአገዛዙ ቅጥረኛ የሆኑ «ሐሰተኛ የኦነሰ ወታደሮች» መኖራቸው የተረጋገጠ እውነታ ነው። የዋሽንግተን ፖስት ምርመራ፣ ከመንግሥት ኃይሎች ጋር ግንኙነት ባለው የቀድሞ እስረኛ የሚመራው የኦነሠን ስም አንግቦ ሲንቀሳቀስ የነበረው ፀረ-አማፂ ቡድን ያለ ሲሆን ይህም በኦነሠ ላይ የሚቀርቡ የዜጎች ጥቃትና ግድያዎችን ሲፈጽም መቆየቱን አረጋግጧል። የሮይተርስ ምርመራ «ኮሬ ናጌኛ» (የደህንነት ኮሚቴ) የተባለውን ሚስጥራዊ ቡድን የኦሮሚያ ከፍተኛ ባለስልጣናትን እንቅስቃሴ ይፋ አድርጓል፣ ይህም ከህግ አግባብ ውጭ ግድያዎችን እና ህገወጥ እስራቶችን ያስፈጸመ፤ ያዘዘም ነው። በወሳኝነት ምርመራው የከረዩ አባ ገዳ ልዑካን ጭፍጨፋ የተቀነባበረው በእነዚህ ባለስልጣናት መሆኑን አረጋግጧል፣ ከዚያም የኦሮሚያ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ግድያዎቹን በኦነሰ እንዲያሳብብ መታዛዙን ኣጋልጧል።
አምነስቲ ሪፖርቱ ውስጥ የጥቃቱ ሰለባዎች ወንጀለኞቹ ማንነታቸውን፤ ኦነሠ መሆናቸውን በግልጽ እንደነገሯቸው ይናገራሉ [ገጽ 15]። ይህ የተላላኪ ታጣቂዎች ተግባር ደምበኛ መለያ ነው። በራሳቸው በሚቆጣጠሩት አካባቢ ውስጥ ትክክለኛ የኦነሠ ተዋጊዎች ወንጀል ሲፈጽሙ ማንነታቸውን አስቀድመው የሚናገሩት ለምንድን ነው? የተገለጸው ባህሪ መንግስት የላካቸውን አስነዋሪ ወኪሎች ግፍ እንዲፈጽሙ ብቻ ሳይኖን ስትፈጽሙ ኦነሠ ነን በሉ ተብሎ የተሰማሩ ለመሆናቸው ትልቅ ማሳያ ነው።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ይህን በሚገባ የተመዘገበ የአገዛዙ ታጣቂዎች እውነታን ሙሉ በሙሉ ችላ በማለቱ፣ ስህተት እየሠራ ብቻ ሳይሆን፤ በአገዛዙ የሚደገፍ ገዳይ ቡድን ስምን በንቃት እያጠበ ጭምር ነው። የመንግስትን ፕሮፓጋንዳ እንደ ሰብአዊ መብቶች ጥናት አድርገው እያቀረቡትም ነው።
2) ባሕሩን የማድረቅ የአገዛዙ ፖሊሲ፡ በሪፖርቱ ችላ የተባለ የአገዛዙ የፀረ ሽምቅ ዶክትሪን
ሪፖርቱ የሴቶችን መፈናቀል እና ቤቶችን ማቃጠልን ይገልፃል። ነገር ግን እነዚህን ድርጊቶች ከኢትዮጵያ አገዛዝ ግልጽ እና ይፋዊ ፖሊሲ ጋር አያገናኝም። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ መሪ የነበረው ፈቃደ ተሰማ “ዓሳዎቹን ለመያዝ ባሕሩን ማድረቅ አለብን” ሲል በይፋ ተናግሯል። ይህ ሲቪሉን ህዝብ (ባህሩን) ለኦነሠ (ዓሣው) የድጋፍ መሰረት አድርጎ የሚቆጥር በይፋ የተገለጸ የአገዛዙ የፀረ ሽምቅ ኦፍስየላዊ ዶክትሪን ነው። በሪፖርቱ ውስጥ የተገለጹት የጅምላ መፈናቀል፣ የቤቶች ማቃጠል እና ማህበረሰቦችን ማሸበር ለኦነሠ ድጋፍ ላደረጉ ሰዎች ለመቅጣት የተደረገ የፖሊሲው ተግባራዊነት መገለጫ ነው።
የአምነስቲ ሪፖርት፣ ለዚህ መፈናቀል ኦነሠን ተጠያቂ በማድረግ፣ የአንድ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣንን ኑዛዜ ወስዶ ለተጎጂዎቹ ክስ እንደማድረግ ነው። የሪፖርቱ የህግ ትንተና፣ «የታጠቀው ቡድን ተዋጊዎች የሲቪል ህዝብን ክፍል ለማፈናቀል የጾታዊ ጥቃት እየተጠቀሙ ነው ብሎ ማመን ምክንያታዊ ነው» [ገጽ 23]፣ የተረጋገጠ ተመሳሳይ ግብ ያለው የተመዘገበ የኣገዛዙ ፖሊሲ በመኖሩ ውድቅ ያደርገዋል።
3) ተዓማኒነቱን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገቡ መሠረታዊ የሐቅ ስሕተቶች
የሪፖርቱ ተዓማኒነት በራሱ መሰረታዊ የሃቅ ስሕተቶች ትብታብ ስር ይወድቃል። ስለ ኦነሰ አደረጃጀት ማንም ተራ ሰው ሊያጣራቸው የሚችላቸውን መሰረታዊ ሃቆችን አያውቃቸውም። ምሳሌዎች፥
· «ኦነሠ አምስት ዋና ዋና ዕዞች አሉት» [ገጽ 11] ፡ ሐሰት። ኦነሰ በኦሮሚያ ስምንት ዕዞች አሉት።
· «የምዕራቡ ዕዝ የሚመራው በጃል ገመቹ አቦዬ ነው» [ገጽ 11] ፡ ሐሰት። ገመቹ አቦዬ የምዕራቡ አዛዥ ሆኖ አያውቅም።
· «የማዕከላዊ ዞን ዕዝ የሚመራው በጃል ጂሬኛ ነው [ገጽ 11] ፡ ሐሰት። ማዕከላዊ ዕዝ ጃል ጂሬኛ በሚባል ሰው አልተመራም።
የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ምርመራ የዕዞቻችንን ብዛት ወይም የአዛዦችን ስም በትክክል ሪፖርት ማድረግ ካልቻለ፣ ጥልቅ ምርምር የሚያስፈልጋቸውን የጦር ወንጀል ብያኔዎች መስጠት እንዴት ይችላል? ይህ የሚያጠኑትን ርዕሰ ጉዳይ መሠረታዊ የሆነ ግንዛቤ አለመኖሩን የሚያሳይና እና በሪፖርቱ ውስጥ ባለው እያንዳንዱ «ግኝት» ላይ ሌላ ተጨማሪ ጥርጣሬን ያስከተለ ሆኖ ተመዝግቧል።
4) የተመረጠ ምልከታ፡ የስርዓቱን ከፍተኛ ጥፋተኝነት መደበቅ
ሪፖርቱ በኦነሠ ላይ ብቻ ያተኮረ መሆኑ ብያንስ እጅግ በጣም አስገራሚ የሆነ የቸልተኝነት ድርጊት ነው። ከዛ ሲያልፍ ደግሞ የኣገዛዙን ወንጀሎች የማጠብ ተግባር ነው። በኦሮሚያ የተከሰተው ጦርነት የአንድ ወገን ጉዳይ አይደለም፤ በርካታ ተዋናዮችን የሚያሳትፍ ጦርነት ሲሆን፣ በተደጋጋሚ በተደረጉ ገለልተኛ ጥናቶች፤ ኣገዛዙ ለሚደርሱ በደሎች ከፍተኛውን ኃላፊነት ይወስዳል።
· የተባበሩት መንግስታት ምርመራ እንዳመለከተው የመንግስት ኃይሎች (የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፣ ፖሊስ እና ተባባሪ ሚሊሻዎች) በ2023 በኢትዮጵያ ውስጥ ከተፈጸሙት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች 70% የሚሆኑትን ጥቃት ፈጽመዋል። ከአመነስቲ የ10 ተጠቂዎች ናሙና ጋር ሲነጻጸር ጥናቱ 7,103 ያካተተ ሲሆን ሁሉም መንግስታዊ ያልሆኑ የታጠቁ ቡድኖች 23% ብቻ ይከሳል።
· የተባበሩት መንግስታት በተጨማሪም በነሐሴ እና ታህሳስ 2023 መካከል ብቻ፣ በመከላከያ ሰራዊቱ የተፈጸሙ 18 የድሮን ጥቃቶች 248 ሰላማዊ ሰዎችን ለሞት እና 55 ደግሞ ቁስለኞች ዳርጎ: ትምህርት ቤቶችን እና ሆስፒታሎችንም አውድመዋል።
· በUN ICHREE የተደረጉ ሌሎች ምርመራዎች የአገዛዙ ኃይሎች በጥቃቶች ውስጥ ያላቸውን እጅግ የጎላ ሚና በተከታታይ አሳይተዋል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል እነዚህን አሃዞች ያውቃል። ይፋዊ ናቸው። ሆኖም የኣገዛዙን ወንጀል ኣጥቦ ሪፖርት ማዘጋጀት መርጠዋል። ይህ ሪፖርቱን የፖለቲካ መሳሪያ እንጂ የሰብአዊ መብቶች ሪፖርት አያደርገዉም።
5) የምርመራ ዘዴ፡ የርቀት ምርምር እና ያልተረጋገጡ ክሶች
አምነስቲ ጥናቱ የተካሄደው በመንግስት በተጣለ የመገናኛ ብዙሃን ኣፈና ባለበት መሆኑን ያምናል [ገጽ 11]። ቃለመጠይቆችን ያደረጉት ከርቀት መሆኑን ይገልጻል[ገጽ 8] ነው።
ከፍተኛ የኣገዛዙ ክት ትል፤ ማስፈራራት እና ፕሮፓጋንዳ ካለበት አካባቢ፣ ከሩቅ በተደረገ ቃለ ምልልስ ላይ የተመሰረተ ጥናት፤ እንድሁም በቦታው ተገችቶ ወንጀለኞችን፣ በቦታው ያሉ ፎሬንሲክ ማስረጃዎችን ለመመርመር ዕድል ሳይኖረው የሚደረግ ጥናት ከመጀመርያዉኑ ትርጉም ያለው መደምደሚያ ላይ ሊደርስ እንደማይችል መገመት አያዳግትም።
ሪፖርቱ የተገነባው በአሸዋ መሠረት ላይ ነው። የተጎጂዎቹ ስቃይ እውነተኛ ነው ብለን እናምናለን፣ ነገር ግን ሪፖርቱን የእህቶቻችንን ፍትሕ በመደበቅ በቁስላቸው ላይ እንጨት ሰዷል። ኃላፊነት የሚሰማው የሰብአዊ መብት ድርጅት፣ «ጥፋተኞቹን ማርጋገጥ ኣልቻልኩም» እያለ፣ እንደዚህ አይነት የወደቀ ሪፖርት ሳያወጣ ቆም ብሎ፣ ጥፋተኞቹን በማረጋገጥ ለእህቶቻችን ፍትሕን በማረጋገጥ በኩል ሚናውን ይወጣ ነበር።
በመሆኑም ከላይ በተጠቀሱት የገዘፉ ጉድለቶች የተተበተበውን ይህንን ምርመራ ተብዬ የፖለቲካ ጥራዝ በማጠፍ እና ይቅርታ በመጠየቅ፤ አምነስቲ አዲስ ምርመራ እንዲያስጀምር ጥሪ እናቀርባለን።
6) ለገለልተኛ ምርመራ ጥሪ
የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ቀደም ሲል በእሱ ስም የተላከኩ ሌሎች በርካታ ከባድ ወንጀሎች ላይ ገለልተኛ ምርመራ እንዲደረግ በተደጋጋሚ ጥሪ አቅርቧል። እነዚህ ጥሪዎች በአብዛኛው በአገዛዙ እና ደጋፊዎቹ ችላ ተብለዋል።
ይህ ገለልተኛ ምርመራን የመቃወም አካሄድ ዓለም አቀፍ የተጠያቂነትን የሚሸሸውን የአገዛዙን ሰፊ ታሪክ እና የፖሊሲ አቋም መሆኑን ያሳያል። በተለይም አገዛዙ በተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት፣ የዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ባለሙያዎች ኮሚሽን በኢትዮጵያ ላይ የተሰጠውን ተልዕኮ እንዲያቋረጥ ያልተቋረጠ የዲፕሎማሲ ዘመቻ አካሂዷል፣ በምርመራ ስራው መካከል መንገድ ላይ አስቁሟል።
ከዚህ ዳራ አንጻር፣ በምዕራብ ኦሮሚያ ውስጥ በተመዘገቡት የቅርብ ጊዜ ክሶች ላይ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የኦሮሚያ ክልል ክፍሎች ውስጥ የተፈጸሙ ከባድ በደሎች ማስረጃዎች ባሉባቸው አጠቃላይ እና በእውነት ነጻ ምርመራ እንዲደረግ ጥሪውን በድጋሚ ያቀርባል። ተጠያቂነት ሊረጋገጥ፣ የተዛባ መረጃ መወገድ እና የተጎጂዎች ክብር እና መብቶች ሊከበሩ የሚችሉት በእንደዚህ አይነት ምርመራ ብቻ ነውናስ።
የኦነግ፡ኦነሠ ከፍተኛ ፅዝ
መጋቢት 6, 2026
