መጋቢት 9, 2024 እአአ የኦሮሚያ ብሔራዊ ሚዲያ (ONM-ABO)
በመላዉ ኦሮሚያ እና በኦሮሚያ አዋሳኝ ቦታዎች በብልፅግና አገዛዝ ዘመን የኦሮሞ ህዝብ በዘመኑ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ስቃይ፣ እንግልት እና ግድያን እያስተናገደ ንብረቱንም እየተዘረፈ ይገኛል። በዚህም መሰረት መጋቢት 4 ቀን 2024 እአአ የፋሽስቱ ብልፅግና መንግስት ታጣቂዎች ከሀረሪ ክልላዊ መንግስት ጋር በመተባበር ‘የከተማ ፕላንን ለመጠበቅ’ በሚል ሰበብ የህዝብ መኖርያ ቤቶችን የማፍረስ ተግባር ላይ ተሰማርተዋል። የድሆችን መኖርያ ቤቶች ማፍረስ በተቃወሙ ዜጎቻችን ላይ በተከፈተ ተኩስ 5 ሰዎች ሲገደሉ በርካቶች መቁሰላቸውን ምንጮች ለኦሮሚያ ብሔራዊ ሚዲያ ተናግረዋል። በዚህም መሰረት ቀመር አብዱ፣ አቡበከር ጌታሁን፣ ለሚ ሙሜ፣ ሙራድ ዮሃንስ እና ባህር የሚባሉ ኦሮሞዎች በግፍ ተገድለዋል። የክልሉ መንግስት የኦሮሞ ተወላጆችን በከተማው ውስጥ በተደጋጋሚ በመሰብሰብ ‘ክልላችሁ እዚህ አይደለም እንዲያዉም እናባርራቿለን’ የሚል ዛቻና ማስፈራራት እየደረሰባቸዉ መሆኑንም ጨምረዉ ምንጮቻችን ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በሰሜን ኦሮሚያ በወሎ ኦሮሞ ላይ የተከፈተዉም ጥቃት እንደቀጠለ ሲሆን መጋቢት 3 ቀን 2024 እአአ የአማራ ጽንፈኛ ሃይሎች ከጨፋ ሮቢት ወደ ፉርሴ ተሳፋሪዎችንና የምግብ እህል ጭኖ ሲሄድ በነበረ ተሽከርካሪ ላይ ተኩስ በመክፈት ሁለት ንጹሃንን እንዳቆሰሉ ምንጮቻችን ገልጸዋል። ‘ኦሮሞን ከወሎ ከመሬቱና ከርስቱ ማፈናቀል’ የሚል መፈክር በማንገብ ባለፉት 5 አመታት ለየት ባለ መልኩ በወሎ ኦሮሞዎች ላይ በዘመተዉ የአማራ ፋኖ ታጣቂ ቡድን ለሞት፣ ለመዘረፍ፣ ለአካል መጉደልና መፈናቀል የተዳርገዉ ሰላማዊዉ ህዝባችን በነዚህ አሸባሪዎች ድርጊት መማረራቸዉም ተዘግቧል። መንግስት ነኝ ባዩ ቡድን አንድም ዝም ብሎ መመልከቱ፣ ህዝቡ ደግሞ ራሱን መከላከል ሲጀምር ጣልቃ መግባቱ፣ በወሎ ኦሮሞዎች ላይ ጫና ማድረጉ የዚህ እኩይ ተግባር ተባባሪ ለመሆኑ ማስረጃ ነዉም ብለዋል።
በተመሳሳይ መልኩ የኢምፖየሯ ታጣቂዎች በምዕራብ ሸዋ ዞን፣ በግንደበረትና ጀልዱ ወረዳዎችም በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት እያደረሱ መሆኑ ተዘግቧል። መጋቢት 4, 2024 እአአ ግንደበረት ወረዳ፣ ዋሻ ቀበሌ፣ ልዩ ስሙ ገባ ደፊኖ በሚባል መንደር ውስጥ በመግባት ሁለት ሴቶችን፣ የአንድ ልጅ እናት የሆነችዉን አዴ ጋዲሴ ዲባባ ባቱና አዴ ቀባኑ ተስፋ ተረፈ በጥይት በመምታት አቁስለዋል። ይህ ዘገባ እስከ ተጠናከረበት ጊዜ ድረስ ተጎጂዎቹ ምንም አይነት ህክምና እንዳላገኙ ታውቋል። በተያያዘ ዜና፣ በዚሁ ዕለት የስርዐቱ ታጣቂዎች ጀልዱ ወረዳ፣ ጎሮ ቀበሌ፣ በመግባት፣ ባይሳ ጣፋ ከተባሉት ኣዛውንት እህልን ጨምሮ ያላቸዉን ንብረት በሙሉ ከነመኖርያ ቤታቸው በእሳት ማዉደማቸዉን ምንጮች ለONM ተናግረዋል።
የስልጣን እድሜውን ለማራዘም የሴራ-ፖለቲካን እንደ ተጨማሪ ስልቱ በማድረግ እየተንቀሳቀሰ ያለዉ የፋሽስቱ አብይ መንግስት አሁን ደግሞ ‘የአማራ ተፈናቃዮችን ወደ ቦታቸው እመልሳለሁ’ በሚል ሽፋን የተመረጡ የአማራ ተስፋፊ ኃይሎችን ከፊንፊኔ ወደ ምስራቅ ወለጋ ዞን፣ ጊዳ አያና ወረዳ፣ ጉትን ከተማ እያጓጓዘ ይገኛል። የአከባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት፣ ኦሮሞ በማንነቱ ብቻ፣ በእነዚህ ወራሪ ኃይሎች እየተጠቃ ባለበት በዚህ ጊዜ ስርዐቱ ባለፉት ሁለት ቀናት ብቻ እነዚህ ተጨማሪ ፀረ-ኦሮሞ አካላትን በማደራጀት በህዝብ መጓጓዣ ተሽከርካሪዎች በመጠቀም ወደ ሥፍራው በማስፈር ላይ መገኘቱ ገዢው መንግስት ለኦሮሞ ህዝብ ያለውን ንቀት ያሳያል ብለዋል። በተደጋጋሚ ከጎጃም ድንበር በመሻገር በምስራቅ ወለጋ ጥቃት ሲፈጸሙ የነበሩና ያሉ ሽፍቶችን በመጠቀም ህዝባችንን ማጥቃትና ማፈናቀል የአብይ መንግስት ሌላኛዉ ሴራ መሆኑ በተደጋጋሚ የተዘገበ ጉዳይ ነዉ።
በሌላ ዜና በዚሁ ዞን ጂማ አርጆ ወረዳ፣ ቃኦ በሚባል ቀበሌ፣ የኢምፓዬሪቱ ወታደሮች ያለምንም ጥፋት ነዋሪውን መደብደብ መዝረፍ እና ማሰር ቀጥለዋል። በዚሁም መሰረት ተካልኝ መንግስቱ የተባለ ወጣት ሲታሰር፣ ኦቦ መሃመድ ሐሰን የተባሉት አዛዉንት ቤት በመሄድ እሳቸውን ስላጡ ባለቤታቸው ሙኒራ ቃስምን ከማሰራቸዉም ባሻገር 2 በሬዎቻቸውን ዘርፈው መሄደቸውም ታውቋል።
የኦሮሞ ህዝብ በዚህ ሁሉ ስቃይና ሰቆቃ ዉስጥ እያለ ከፋሽስቱ የብልጽግና መሪና ቡድን ጋር ተጎዳኝተው የሚሰሩ አካላት በሙሉ የወንጀሉ ተባባሪዎች መሆናቸዉን ሊያዉቁት እንደሚገባ ማስገንዘብ እንፈልጋለን።
የኦሮሚያ ብሔራዊ ሚዲያ (ONM-ABO)
