ሰኔ 23፣ 2024 አራት ቢዮሌሳ ኦሮሚያ (ONM-ABO)
የኦሮሞ ህዝብ በከባድ ባርነት ውስጥ እና የመብት ጥሰት ሰለባ ሆኖ ለመኖር ከተገደደ 150 ዓመት አልፎታል። ይህንንም ዘመን ያለምንም መታከት አልገዛም ብሎ ኃብት ንብረቱን በትኖ የነፃነት ትግል ቢያካሂድም ደሙ ከመፍሰስ፣ አጥንቱን ከመከስከስ እና ሕይወቱን መሰዋዕት ከማድረግ ውጪ የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ ትክክለኛ መልስ ሳያገኝ ቆይቷል። ይኸውም የፖለቲካ ባለስልጣናት ስልጣን ከተቆናጠጡ በኋላ የኢምፓየሪቱን እድሜ ለማራዘም፣ የኦሮሞ ህዝብን የነፃነት ጥያቄ ለማጨናገፍ እና ህዝቡን ለማንበርከክ ህዝቡን ከቀዬው ማፈናቀልን፣ መዝረፍ፣ ማሰር፣ መደብደብ እና መግደልን ያካሂዱ ስለነበረ ነው።
7ኛው የኢምፓየሪቱ ንጉስ ኮሎኔል አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ሲመጣ የኦሮሞ ህዝብም ሆነ፣ የፖለቲካ ለውጥ ፈላጊ ብሔር ብሔረሰቦች ትግሉ እንዲታፈን ሳይሆን፣ የፓለቲካው ማህደር ሰፍቶ በኢምፓየሪትዋ ለመጨረሻ ግዜ የተሻለ የፖለቲካ አመለካከትም ሆነ ውሳኔ ይመጣል ብለው ተስፋ ነበራቸው።
ነገር ግን እንደ እስስት ከሚለዋወጠው ፊቱ ጋር ባህሪውም እንደ ድርጊቱ እየተቀያየረ ለህዝቡ የገባውን ቃል ከመፈፀም ይልቅ ስልጣኑን ለማጠናከር ወታደሩን ከህዝብ ዘብነት ወደ ግል ጠባቂነት በመቀየር የጦር መሳሪያ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ገዝቶ ሰላማዊ ህዝብን ብቻም ሳይሆን የቤት እንሰሳን እያስጨፈጨፈ እና ቤት ንብረት በእሳት እንዲያወድሙም እያደረገ ይገኛል። ለፕሮፖጋንዳ ለሚጠቀምባቸው ሚዲያዎቹ እና በማህበረሰብ ሚድያ ላይ ፕሮፖጋንዳ እንዲሰሩለት ለቀጠራቸው በሚሊዮን የሚቆጠር የእሜሪካ ዶላር አውጥቶ አሰማርቷል።
የተጨቆነው ህዝብ፦
- እውነተኛ ነፃነትን ይፈልጋል።
- ምኞቱም ሉዓላዊት ሐገሩን መጎናፀፍ ነው።
- ፍላጎቱ የራሱን ዕድል በራሱ በመወሰን ነፃ የሆነችውን ሐገሩን መገንባት ነው።
ይህ አመለካከት በተለይ ከኦሮሞ ህዝብም ይሰማል። በኦሮሞ ነፃነት ትግልም ውስጥ ይህ ከፍ ብሎ ይነገራል። የኦሮሞ ነጻነት ትግል መርሃ ግብሩ፣ እስትራቴጂው እና ስልቱም በዚሁ የተካነ ነው። የኦሮሞ ህዝብ የነፃነት ትግሉ ግብና ዓላማ በግልፅ ከአብራኩ ወጥተው የሚታገሉለት ልጆቹ በፕሮግራም ቀርጸው ማስቀመጣቸው ተጠቃሚ ሆኖዋል።
የኦሮሞ ህዝብ ለዘመናት ሲያካሂድ የነበረው ትግል በስኬት ሊያጠናቅቅ ደርሶ፣ ህወሃት/TPLF ያሳደገው አፈ ጮሌው ኮሎኔል አብይ አህመድ ለጭቁን ህዝብ የቆመና ብሔርተኛም በመምሰል ወንጀለኛነቱንም በማር ተለዉሰው በሚወጡት ቃሎቹ በመደበቅ ስልጣኑን ተቆናጠጠ። ስልጣኑንም ተደላድሎ ከያዘ ግዜ ጀምሮ የኦሮሞን ህዝብ ማሰቃየት አጠናክሮ ቀጥሏል። በዚህም ድርጊቱ ኦሮሚያን እስከ ዛሬ ድረስ የደም ገምቦ እንድትሆን ሲያደርጋት፣ ይቅር የማይባል የከፋ ግፍንም በመፈፀም ላይ ይገኛል። ይኸውም የሰላማዊ ዜጎች ግድያ እየጨመረ መሄድ፣ እስር ቤቶች የኦሮሞ ህዝብ መኖሪያ ቤት መምሰል፣ ንብረት መዝረፍ፣ ቤቶችን ከነንብረታቸው በእሳት በማውደም ህዝቡን ከቀዬው ተፈናቅሎ የጎዳና ተዳዳሪ መሆንንም ይጨምራል።
ቀጣፊው/እዉሸታሙ አብይ አህመድ በኦሮሞ ህዝብ ስም ስልጣኑን ከያዘ እና ስልጣኑንም በደምብ መቆጣጠር ከጀመረበት ግዜ ጀምሮ የኦሮሞ ህዝብ የኑሮ ደረጃ ተበላሽቷል። የኦሮሞ ህዝብ ወደ እስር ቤት ተጋዘ። ከቀዬውም ተፈናቀለ፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩም ተገደሉ።
ባለፈው አርብ ሰኔ 14፣ 2024 የተባበሩት መንግሥታት ሰብዓዊ ኮሚሽን የኦሮሚያን ሁኔታ በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ላይ በ2023 ኦሮሚያ ውስጥ 366 ሰዎች ተገድለዋል ብሏል። ከእነርሱም ውስጥ 46ቱ ሴቶች መሆናቸውን ገልጿል።
ይህ የተባበሩት መንግሥታት ሰብዓዊ ኮሚሽን የሰብዓዊ መብት ጥበቃ መግለጫ የተመረኮዘው ከነሐሴ እስከ ታህሳስ 2023 ድረስ የነበረው ጭፍጨፋ ላይ ነው። ይኸውም 18 የድሮን ጥቃቶች እንደነበሩና በዚሁ ጥቃት 248 ሰዎች ሲገደሉ 55 ደግሞ መቁሰላቸውን አትቷል።
ይህ የሟች እና የቁስለኞች ቁጥር በተወሰነ ወራት እና ድርጊት ላይ የተፈፀመ እንጂ በእያንድንዱ የኦሮሞ ህዝብ ቀዬ የተከሰተን አያካትትም። የኮሚሽኑ የበላይ አመራር ቮልካን ቱርክ ለዜጎች ጥበቃ እንዲያደርግና ሰላም እንዲያወርድ ቢጡይቁም ህዝቡን ማሰር፣ መግደል፣ መዝረፍ እና ቤቱን ከነንብረቱ ማቃጠሉን አባብሶ ቀጥሏል።
ይህም ድርጊት የሚፈፀምበት ምክንያት አብይ አህመድ የኢምፓየሪትዋ ገዢና የብልፅግና ቡድን መሪ እውሸታም እና ለሚመራው ህዝብ ደንታ የሌለው፣ ስልጣኑን ለማጠናከር እየሰራም እንደሆነ ይታወቃል።
የአሜሪካን እና ኤዉሮፕያውያንን ቃል ተቀብሎ ስልጣኑን በመቆናጠጡ የአለምን ህዝብ በማጭበርበርም የሰላም ኖብል ሽልማትም ተለግሷል። በአስተዳደጉም በተለይም ሕወሀት እጅ ውስጥ ከገባ ጀምሮ ስልጣን ለመጨበጥ አእምሮውን በተለየ መልክ መቅረፅንም ሲማር፣ ሲያስተውልና የስልጣን ደባዎችንም እንዴት እውን እንደሚያደርግ ሲሰራበት የነበረ በመሆኑ ስልጣን ከያዘበት ግዜ ጀምሮ ይህንኑ ተግባር ለሚፈጽሙለት ስልጠና ሲሰጥና እየሰጠም ይገኛል። ስልጠናውም ህብረተሰቡን በተለያየ ስልት ከቀዬው ማፈናቀል፣ መዘረፍና ማዘረፍ፣ ግጭት መፍጠር፣ ስዎችን ማሰቃየት፣ አረመኔያዊ የአገዳደል ሰልትንም ይጨምራል።
አብይ አህመድ የእውነት መሪ አለመሆኑን እና በሁለት የተለያየ ገፅታ ህዝቡን እየመራ እንደሆነ በአለም ደረጃም እየተነገረ ነው።
ስልጣን እንደያዘም በ2018 የዜና አውታሮች (ሚድያ)፣ የታወቁ ጋዜጠኞች ሳይቀሩ ቶማስ ሰንካራንም በመርሳት አብይን የለውጥ፣ ተራማጅ እና ወጣት መሪም እያሉ ሲያሞካሹትም ነበር።
ሆኖም ግን ይህንኑ በተናገሩበት አንደበትና የዜና አውታራቸው ዛሬ “የሰላም ኖብል ተሸላሚው ላውሬት ጦርነትን አወጀ!” “ህዝቡን ገደለ።” “የጦር ግንባር ላይ ጥቃትን ፈፀመ።” በማለት እና ወንጀሎቹንም ዘርዝረው ሲያጋልጡ እየተመለከትን ነው። ብዙ የዜና አውታሮችና ጋዜጠኞች በስራቸው ሃፍረትም እየተሰማቸው ነው።
ቶም ጋርድነር የ “Economist” ጋዜጠኛ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ሲሰራ የነበረ እና በትግራይ ጦርነት ግዜ ከኢትዮጵያ የተባረረው በቅርቡ ባሳተመው መፅሀፉ፥ “የአብይ ፕሮጀክት፥ እግዚአብሔር፣ ኃይል/ጉልበት እና ጦርነት በአዲሲቱ የኢትዮጵያ” ውስጥ አብይ አህመድ ቀጣፊ፣ ማነቱንና አቅዋሙን በየግዜው የሚቀያይር፣ እንዲሁም ምንም ዓይነት ህዝብንና ሐገርን የሚመራበት ፖሊሲ የሌለውና ወታደራዊ መንግስት መሆኑንም ይገልፃል።
በአሁኑ ወቅት ኢምፓየሪትዋ የከፋ ችግር ውስጥ ትገኛለች። ፖለቲካዊ መግባባት በመጥፋቱ የኢምፓየርዋ ኢኮኖሚ ወድቋል፣ መሬቱም የጦርነት አውድማ በመሆኑ የአባቶች፣ የህፃናት፣ የእናቶችና የወጣቶች ሞት የሚታይበት ሆኖዋል።
ኢምፓየሪትዋ በተሳሳተ መንገድ ላይ እንዳለች በመገንዘብ ትክክለኛ አቅጣጫ እንድትይዝ አቋም መውሰድ ሲገባው አብይ አህመድ አሁንም እውሸትና ፕሮፖጋንዳውን በመጠቀም የጦርነት ዕቅድ አውጥቶም ጦርነቱን እያካሄደ ይገኛል።
ባለራዕይ መሪዎች የህዝባቸውን ፍላጎት ተመርኩዘው ወቅታዊና የወደፊት ጥቅምንም በመተንተንና በማመዛዘን በስርዓት ይመራሉ። የህዝቦችን አንድነት ማጠናከር ጠቀሜታው ለፖለቲካዊ መግባባት፣ እኩልነት፣ ዴሞክራሲና ኤኮኖሚያዊ እሴቶችንም በነፃነት እንዲጠቀሙ ያደርጋል።
እንደ አብይ አህመድ አይነቱ አምባገነን መሪ ግን የኦሮሞን ህዝብ “የአጭር ዘመን አስታዋሾች” “short memorian” እያለ በማፌዝ ህዝባችንን የኮሎኒያሉን ስርዓት እያራመዱ በነበሩት መሪዎች ያላየውን የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈፀመበት ይገኛል።
ባለራዕይ መሪ የሚጠቅመው ሐገሩን ብቻ ሳይሆን በአካባቢው የሚገኙትን ሐገሮች (በቀጠናው) እና አለምንም ጭምር ነው። እንደዚህ አይነት መሪ ለመኖር ካለው ጉጉት አንድ አንድ ግዜ ከባድ ተግዳሮቶችን ለመቋቋም ፈቃደኛ ባይሆንም ለሐገሩና በቀጠናው ችግር አይፈጥርም። ከባድ ፈተናና እንቅፉቶች እንደዚህ ካሉ መሪዎች ፊት ይጠፋሉ፣ በተፃራሪ መንገድ ግን ራዕይ የሌላቸው መሪዎች ፊት ይታያሉ።
ስለዚህም አብይ አህመድ ለኦሮሞ ህዝብ ፍትሃዊ፣ ትክክለኛና እውነትን የተመረኮዘ ራዕይ ስለሌለው ህዝቡን በፖለቲካ አመለካከት እየከፋፈለ፣ በሃስት እየወነጀለ፣ እያሳሰረ፣ እያስገደለ፣ ቤት እና ንብረቱን እያስወደመ ይገኛል። በኢኮኖሚውም ዙሪያ ኦሮሞ ሚና የለውም። የኦሮሞ ገበሬዎች ቀዬም ፖለቲካን ምርኩዝ አድርገው በተኩስ እሩምታ እየተናወጠ በመሆኑ አርሶ ለቤተሰቡ የምግብ ፍጆታ የሚያሟላው በቁጥር በጣም ትንሽ ነው። አርሶ አደሮች ይገደላሉ፣ በህይወት ያሉት ቤት ንብረታቸውን ትተው በሽሽት ላይ ሲሆኑ የመኖር ሕልውናቸውም አደጋ ላይ ነው፣ ተማሪዎች ትምህርታቸውን አቋርጠው የስራ አጡ ቁጥር በጣም ጨምሮዋል። ኤኮኖሚው ከባድ ጫና ላይ ስላለ እና ስራም ማግኘት ስላልተቻለ ብዙዎች ለስደት ተዳርገዋል።
ባለፈው ሳምንት 260 ስደተኞች ከሶማሊያ በየመን በኩል ወደ ሳውዲ አረቢያ በመርከብ እየተጓዙ ባህር ውስጥ ሰምጠዋል። ከእነዚህም ውስጥ 145 ኢትዮጲያውያን ሲሆኑ፣ በሚያዚያ ወርም 60 ሰዎች በጅቡቲ በኩል ሲጓዙም ሰምጥመው ሞተዋል።
ከእውነት የራቀውና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሚነገረው የኤኮኖሚ ስሌት ጠቅላላ ዕድገት (GDP) ምርትንና የገበያ ሽያጭን ይመለከታል። ይህም የኢምፓየሪትዋ የኤኮኖሚ እድገት በምድር ላይ ያለውን እውነታ አያንፀባርቅም።
በአሁኑ ወቅት ህዝቡ የፖለቲካ ለውጥ እንጂ የእነርሱን እውሸት አይፈልግም። የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ትላንት የሕወሓትን መሪዎች “የቀን ጅብ” እያሉ ከአብይ አህመድ ጋር ከበሮ ሲደልቁ የነበሩት ዛሬ “የሐገር ሉአላዊነት ማስከበር” በሚል መርሆ በኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ሰበብ የኦሮሞን ህዝብ ቀዬውን በእሳት በማቃጠል ላይ ሲገኙ፣ ከ2018 በፊት የነበረውን የEPRDF አስተዳደር ለምን አንመለስም እያሉ ፓርላማ ላይ እያወሩ ይሰማሉ።
በእውሸት ሰብሮና ከምድረ ገፅ ለማጥፋት ቢሞክርም እምቢ ያለን የኦሮሞ ህዝብ ስልጣኑንም አጠናክሮ ለመቀጠል የሚፈልግ በዉዴታ ስልጣኑን አይለቅም።
ፕሮፌሰር መሐመድ አባ ጀበል ዛሂሮ ከአራታ ቢዮሌሳ ኦሮምያ ጋር የፖለቲካ ትኩርት (Qorqorti Siyaasaa) በሚባለ ፕሮግራም ባደረጉት ቃለ ምልልስ ውስጥ የሚከተለውን ብለዋል፦
“ኦሮሞ በኢምፓየሪትዋ ውስጥ ባለበት ግዜ ያተረፈው ነገር ቢኖር፥ ቋንቋውን በሚናገሩ የድሮዎቹ ኦሄድድ፣ ኦዲፒ እና የዛሬዎቹ የብልፅግናው ቡድኖች መታሰር፣ መገደል፣ መደብደብ፣ መዘረፍ እና ከቀዬአቸው መፈናቀል ስለሆነ ይህ ደግሞ በመንቃትና በመታጠቅ ከላያችን ላይ መገርሰስ ይኖርብናል። የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት በጀግንነት፣ በቆራጥትነት እና በጽናት ትግል ላይ እንደሚገኝ ሁሉ፣ ማንኛውም ኦሮሞ የሉዓላዊነት መብቱን ማስከበር የሚፈልግ፣ ለነፃነት እና ሉዓላዊ ኦሮሚያን ለመመስረት የሚሰራ ሁሉ ይህንንም እውን ለማድረግ በአንድነት ትግሉን አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። ይኸውም የብልፅግናውን አመራር እና ኢምፓየሪቱን ከትከሻው ላይ በማራገፍ የራሱን ሐገር ኦሮሚያን መቆጣጠር አለበት በማለት መልዕክቴን እቋጫለሁ።”
“ለስልጣኑ ሲል ህዝቡን እየዋሸ የሚኖረው አብይ አህመድ” – ከአራታ ቢዮሌሳ ኦሮሚያ ባለሞያዎች: በጉዮ ጃርሶ ሰኔ 17፣ 2024 በአቢኦ የቀረበ
ድል ለኦሮሞ ህዝብ !!
