ለዘመናዊ መንግሥት አስፈላጊነት ዋና ዋና ምክንያቶች መካከል፣ በገበያ ጉድለት (market failure) ምክንያት የሚፈጠሩ ክፍተቶችን ለመሙላት ተብሎ በተወሰኑ መሰረታዊ ልማት ሥራዎችን ለመስራት ጣልቃ መግባት አንዱ ነው። እነዚህ ሥራዎች ኃላፊነት ባለው መንገድ ሲታቀዱና ሲፈጸሙ የሕዝብ ደህንነትን፣ የኢኮኖሚ እድልን እና ማህበራዊ ትስስርን ያበረታታሉ። ነገር ግን፣ የህዝብ ሀብትን ለመበዝበዝ፣ ማህበረሰቦችን ለማፈናቀል እና ሊያገለግላቸው ይገባ የነበረውን ህዝብ ወይም ማህበራዊ መዋቅራቸውን ለመበታተን ፕሮጀክቶች መሣሪያ ሲሆኑ፣ ፕሮጀክቶቹም ሆኑ የሚያስተዳደራቸው መንግስት ትልቅ እዳ እና ሸክም ይሆናሉ።
በቢሾፍቱ አካባቢ የተጀመረው የአቡሴራ አየር ማረፊያ ፕሮጀክትም ይህንን አጥፊ ሞዴል ተከትሏል።
በዚህ ፕሮጀክት ከሰባት ቀበሌዎች ከ 3000 በላይ አባወራዎች በግዳጅ ተፈናቅለዋል። ከእነዚህ ቤተሰቦች ውስጥ አንዳቸውም በሌላ ቦታ ኑሮን እንደገና ለማቋቋም የሚያስችል ካሳ ወይም እርሻን ለመቀጠል የሚያስችል ምትክ የእርሻ መሬት አልተሰጣቸውም። እያንዳንዱ ተፈናቃይ ቤተሰብ መሬቱን፣ የኑሮ ገቢውን እና የኢኮኖሚ ደህንነቱን ተነፍጓል።
ከጠቅላላው የተፈናቀሉ ነዋሪዎች መካከል፣ በግምት 1,200 የሚሆኑ ቤተሰቦች ብቻ (40 በመቶ የሚሆኑት) – ምትክ መኖሪያ ቤት ያገኙ ሲሆን፣ በዚህ ምክንያት አብዛኛዎቹ ተፋናቃዮች ሙሉ በሙሉ ያለመጠለያ ለመቀረት ተገደዋል፣ በራሳቸው መንገድ ለራሳቸው መጠለያ እንዲፈልጉ ተበይኖባቸዋል።
መኖሪያ ቤት በተቀበሉት ተፋናቃዮች እንኳን፣ ሁኔታዎች አስከፊ ናቸው። በተከታታይ የደረሱን ምስክርነቶች እንደሚያስረዱት፤ ቤቶቹ ደረጃቸውን ያልጠበቁ እና ያልተጠናቀቁ እንደሆኑ፣ መሰረታዊ አገልግሎቶችን የሚሰጡ መዋቅሮች የሌሉበት፣ የቤት ቁሳቁስ እና አስፈላጊ መሠረተ ልማቶች ያልተሟሉላችው መሆኑን ይገልጻሉ። እነዚህ ቤቶች ክብር ያለው ኑሮን ወደነበረበት ለመመለስ ከሚያስችሉ መኖሪያ ቤቶች ጥራት በጣም ያነሱ ናቸው። ይህንን ኢ፡ፍትሃዊነት የሚያባብሰው፣ ተቀባዮች ህጋዊ የባለቤትነት ማረጋገጫ ያልተሰጣቸው መሆኑ፣ ይህም ለመፈናቀል እና ለተጫማሪ ብዝበዛ ተጋላጭ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።
እነዚህ እውነታዎች ቢኖሩም፣ የአገዛዙ የውስጥ ምንጮች እንደሚያሳዩት ለእነዚህ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ በግምት 30 ቢሊዮን ብር የተመደበ ሲሆን – የአንድ ቤት በግምት 25 ሚሊዮን ብር ይሆናል። በግልጽ የሚታየው ጥራት የሌላቸው እና ያልተሟሉ የመኖሪያ ቤቶቹ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ከተመደበው ሀብት ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ገንዘብ አግባብ ባልሆነ መንገድ እንደተመዘበረ እና ለግል ጥቅም እንደዋለ ግልጽ ነው። ይህ ድንገት ወይም በአጋጣሚ የተፈጸመ ምዝበራ ሳይሆን የልማት ፕሮጀክቶች ሆን ተብሎ የተነደፉበት እና የሚተገበሩበትን ስርዓትዊ አሠራር የሚያንፀባርቅ ነው። ይህ ከፍተኛ መጠን ያለው ዝርፊያ እና የህዝብ ሀብትን ለፖለቲካ ካድሬዎች፣ ለታማኞች እና የአብይ አህመድ ወዳጆች ለማስተላለፍ ያስቻለ ነው።
ዝርፊያ የእነዚህ ፕሮጀክቶች አሳዛኝ ውጤት ሳይሆን፤ ይልቁንም ፕሮጀክቶቹ እራሳቸው እንዲህ ዓይነቱን ስርቆት በልማት ሽፋን ለማስቻል የተዋቀሩ ናቸው።
የተፈናቀሉ አርሶ አደሮች የሚያጋጥማቸው ሁኔታ የበለጠ አስደንጋጭ ነው። ያለ ልዩነት የተፈናቀሉ ቤተሰቦች ሁሉም አማራጭ የኑሮ መተዳደሪያ ለማቋቋም ካሳ ወይም ምትክ መሬት ተነፍገዋል። መጠለያ ያገኙትም እንኳ፤ ኑሮዋቸውን የሚመሩበት ምንም አይነት የገቢ መንገድ የላቸውም። ከመሬት፣ ከእርሻ መሳሪያ እና ሀብታቸው ተፈናቅለው ሁሉም የኑሮ መንገድ የተነፈገ ገበሬ በኦና የብሎኬት ክምር ውስጥ ብቻውን መኖር አይችልም። ከስርዓቱ ጋር ግንኙነት ያላቸው የካድሬ ኔትወርኮች ተፋናቃይች ላይ በግልጽ የተስፋ መቁረጥ ስሜቶች እና ድባቦችን እየፈጠሩ፤ ቤተሰቦች የተመደቡላቸውን ቤቶች እንዲሸጡ እና አካባቢውን እንዲለቁ ጫና እያደረጉባቸው ይገኛሉ። ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት የመሬት ደላላዎች ተፈናቃዮቹን ፍርሃት ውስጥ በመክተት ቤቶቹን በችግር ግዜ ርካሽ ዋጋ ለመግዛት እያንዣበቡባቸው አነስተኛ ዋጋ እያቀረቡ ይገኛሉ። ቤቶቹን በተመለከተ የባለቤትነት ማረጋገጫዎች ለተፈናቃዮቹ አለመሰጠቱ ደግሞ ነዋሪዎችን ለማስፈራራት እና በህግ ወጥ የመንደር ውል እንዲሸጥ ለማስገደድ ሆን ተብሎ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው። ይህ አካሄድ በዚሁ ከቀጠለ፣ ሊገመት የሚችለው ውጤት ግልጽ ነው፡ ሁሉም የተፈናቀሉ ቤተሰቦች በመጨረሻም ያለ መጠለያ፣ ያለ መቋቋሚያ ካሳ ወይም የኑሮ መተዳደሪያ ገቢ ይቀራሉ ማለት ነው።
የአቡሴራው አየር ማረፊያ ፕሮጀክት ከማፈናቀልና ከምዝበራ ሙስና ባሻገር፣ ድብቅ የፖለቲካ ዓላማ ያለው ነው።
እንደሚታወቀው አንድነቱ የጠነከረ፣ የተባበረ የኦሮሞ የፖለቲካ ግንባር በአገዛዙ ላይ የህልውና ፈተና እንደሚፈጥር አብይ አህመድ በተደጋጋሚ አሳይተዋል። ይህ ፕሮጀክት ኦሮሚያን ወደ ትናንሽ ክልሎች አዋቅሮ ለመበታተን፣ እና ከሌሎች ሀይሎች ጋራ የተባበረ የፖለቲካ ተቃውሞን እንዳይጠነክር ለማዳከም ከሚደረጉ ስትራቴጂካዊ እኩይ ተግባሮቹ አንዱ ነው።
ይህ የአገዛዙ ዓላማ ቀደም ሲል በተለያዩ ዘዴዎች ሲተገበር የቆየ ሲሆን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ፣ ኦሮሚያን ወደ ንዑስ ክልሎች ከፋፍሎ ምዕራብ፣ ደቡብ እና ምስራቅ ክላስተር እያለ በመከፋፈል፣ እያንዳንዱ ክላስተርም ከምን ግዚውም በላይ በማእከላዊው መንግስት ቁጥጥር ስር እንዲሆን አድርጓል። የህግ ማዕቀፍ የሌላቸውና
መደበኛ ያልሆኑ የአስተዳደር መዋቅሮችም እየበረከቱ መጥተዋል። ይህ ለረጅም ግዜ ተንዶ ወረቀት ላይ ብቻ የቀረውን ሕገ መንግሥታዊ ፌዴራሊዝም ላይ የተቃጣ ጥቃትን የሚመለከት ብቻ ሳይሆን የኦሮሚያን ጂኦግራፊያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ትስስር ለማፍረስ በአገዛዙ የሚሰራ የድብቁ ዓላማ ጥረት አካል ነው። የሚፈርሰው የአርሶ-አደሩ በእርሻ መሬት ላይ የተመሰረተ ኑሮ ወይም የኑሮ መተዳደሪያ ብቻ ሳይሆን እራስን በራስ የማስተዳደር፣ ተባብሮ አገዛዝን የማስወገድ የህዝቡ ዐቅም መሠረትም ጭምር ነው።
ስለዚህ፣ በጥቅሉ የአቡሴራ አየር ማረፊያ ፕሮጀክት ማለት፤ የዝርፊያ፣ የከፍተኛ ሙስና እና የተወሰኑ ልሂቃንን ለማበልጸግ እና ኦሮሞን እንደ ህዝብ ተባብሮ አገዛዝን የማስወገድ ዐቅም ለማዳከም የተነደፈ ድብቅ ፖለትካዊ ግብ ያለው ፕሮጀክት ነው። በመሆኑም፣ ለሚመለከታቸው አካላት ሁሉ፣ የአካባቢው ማህበረሰቦች፣ የሲቪክ እና የዓለም አቀፍ ተዋናዮች ይህ ፕሮጀክት በትክክል የልማት ዓላማ የሌለው መሆኑ ታውቆ ለአገዛዙ የሚደረጉ ሁሉንም የፖለቲካ፣ የቴክኒክ እና የገንዘብ ድጋፎችን እንዲያቆም ጥሪ እናቀርባለን።
የኦነግ-ኦነሠ ከፍተኛ ዕዝ
ጥር 22፣ 2026
