• Fri. Apr 26th, 2024

በምዕራብ ወለጋ፣ ቶሌ አካባቢ የአብይ መንግሥት ሚሊሺያ ያደረሰውን እልቂት በሚመለከት:- የኦነግ-ኦነሠ መግለጫ

Jun 20, 2022

በምዕራብ ወለጋ፣ ቶሌ አካባቢ የአብይ መንግሥት ሚሊሺያ ያደረሰውን እልቂት በሚመለከት
(የኦነግ-ኦነሠ መግለጫ)

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ አካባቢ ቶሌ መንደር በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈፀመውን ግድያ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር —የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነግ-ኦነሠ) በጽኑ ያወግዛል። አምባገነኑ የአብይ አገዛዝ የተሳሳተ መረጃ በመፈብረክ እና የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ በማካሄድ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊትን በማጠልሸት ተግባር ቢጠመድም፣ ሠራዊቱ እንደ ፖለቲካ አካልና እና የነጻነት ትግል መሪ የኦሮሞን ህዝብ በተከታታይ አፋኝ አገዛዞች ከሚደረስበት ዘርፈ ብዙ ስቃይ ለማላቀቅ የሚያደርገውን ትግል ከግብ ለማድረስና፣ ዘላቂ ሰላምን በቀጠናው ለማረጋገጥ ከምንጊዜውም በላይ ቁርጠኛ በመሆን ትግሉን በላቀ የሞራል፣ የፖለቲካ እና ወታደራዊ ደረጃ በማፋፋም ላይ መሆኑን በድጋሚ ያረጋግጣል።

ሠራዊቱ በአፍሪካ ቀንድ በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች ሁሉ ባልታጠቁና እራሳቸውን መከላከል በማይችሉ ንፁሀን ዜጎች ላይ በማነጣጠር የሚያተርፈው አንዳችም ፖለቲካዊም ሆነ ወታደራዊ ግብ እንደሌለውም በተደጋጋሚ የገለጸ ሲሆን፣ ይሄንኑ ዛሬም ደግሞ ያረጋግጣል። የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት የሚመራው በኦሮሞ ህዝብ ስነምግባር የታነፀ ወይም የሰፉ (safuu) መርህ ከመሆኑም በላይ በአሸናፊነት የሞራል ልዕልና የሚንቀሳቀስ በመሆኑ የዚህ አይነት የፈሪዎች ተግባር በፍፁም እኛን እንደማይገልፅ ወዳጅም ሆነ ጠላት ሊያውቀው ይገባል:: ተደጋግሞ እንደተገለጸው የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት የሚዋጋው ዛሬ ላይ በአብይ አህመድብልፅግና ፓርቲ የሚመራው አፋኝና ጨፍላቂ ስርዓትን እንጂ የትኛውንም ግለሰብ፣ ቡድን ወይም ማህበረሰብ አይደለም። ኦሮሞም ሆኑ ኦሮሞ ያልሆኑ ሰላማዊ ዜጎችን መሰረታዊ መብቶችና ከሁሉም በላይ የሰውን ልጅ የተከበረ ህይዎት ለመጠበቅ በህይወታችን ጭምር ዋጋ ከፍለን በምንችለው አቅም የሚጠበቅብንን እያደረግን እንገኛለን:: ዛሬም ነገም ይሄንኑ እናደርጋለን::

የአብይ መንግስት ግን በሰላማዊ ዜጎች ላይ ለሚፈጽመው ማንኛውም የግፍ ወንጀሎች ኦነግን እንደ መያዣ እንደሚጠቀም ለማንኛውም የቅርብ ተመልካች ግልፅ ከሆነ ሰንብቷል:: ከነዚህ ወንጀሎች ብዙዎቹ ስፋትና ጥልቀታቸው እየጨመሩ ባሉ መረጃና ማስረጃዎች ፍፁም ለመካድ በሚያዳግት መልኩ እየተረጋገጡ ሲመጡ፣ አገዛዙ በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በኩል በተዘዋዋሪ አምኗል። ብዙውን ጊዜ ገዥው ቡድን የኦነሠን ስም ለማጠልሸት ብቻ ሲል በሌላ ጊዜ ደግሞ የተፈፀመን ሌላ ወንጀል ለማስረሳትና የህዝብን እይታ አቅጣጫ ለማስቀየር በሰላማዊ ሰዎች ላይ የታለመ ግን ያልተቆጠበና ለማመን የሚያዳግት ጥቃት ይፈጽማል። ከቅርብ ጊዜ ትዝታ መጥቀስ የሚጠቅመን ከሆነ በከረዩ የገዳ ሽማግሌዎች በመንግሥት የተፈፀመውን አሰቃቂ ግፍ መጥቀስ ይበቃል።

አሁንም በምዕራብ ኦሮሚያ በቶሌ አካባቢ የደረሰውም እልቂት በይዘቱ ከዚህ የተለየ አይደለም። አገዛዙ ከመደበኛ የፀጥታ ሀይሉ ባሻገር “ጋቻና ሲርና” (የሥርአቱ ጋሻ) የተሰኘ የሚሊሺያ ቡድን ባለፉት ጥቂት አመታት ያደራጀ ሲሆን የዚህንም ህቡዕና አረመኔ ቡድን አባላት አርቴፊሻል ዊግ በማልበስና የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት አባላትን በማስመሰል ኦነሠ በሚንቀሳቀስባቸው የኦሮሚያ አካባቢዎች አሰቃቂ ወንጀሎችን በማስፈፀም እየተጠቀመባቸው ይገኛል። ከላይ እንደገለፅነው አገዛዙ በሚፈጽማቸው እነዚህ ወንጀሎች ሁሉ ዋነኛው ግቡ የኦነሠን ሥምና ዝና ማጠልሸት ቢሆንም፣ አሁን በቶሌ ላይ የደረሰው ጥቃት ግን ሌሎች ልዩ ዓላማና ግቦችም አሉት።

ከነዚህም ግቦች መሀከል የሚከተሉትን መጥቀስ አስፈላጊ ይሆናል::

1ኛ. በቅርቡ በጋምቤላ ዋና ከተማ የኦነግ እና የጋምቤላ ነፃነት ግንባር የወሰዱት የተጠና እና በፍፁም ወታደራዊ የነበረ ጥምር ዘመቻ በድል ከተጠናቀቀ በኋላ አገዛዙ በጋምቤላ ከተማ ነዋሪ የኦሮሞ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ አሰቃቂ የዘር ማጥፋት በመፈፀም የተለመደ የአጸፋ ጥቃቱንና የወደቀ ብቃቱን አሳይቷል:: አሁንም በቀጣይነት በመፈፀም ላይ ይገኛል። የጋምቤላ ልዩ ሃይል፣ የፌደራል ፖሊስ እና ተባባሪ የጸጥታ አካላት የኦሮሞ ንፁሃን ዜጎችን እያደኑ ከህግ አግባብ ውጭ በጠራራ ፀሀይ ገድለዋል አሁንም ቤት ለቤት በመሄድ እየገደሉ ነው። ይህ በጋምቤላ የኦሮሞ ሰላማዊ ዜጎች ላይ የተፈፀመውንም ፋሺስታዊ ግድያ የሚያሳዩ ማስረጃዎች ማህበራዊ እና መደበኛ ሚዲያዎች ላይ በብዛት እየተሠራጩ ይገኛሉ። በተጨማሪም በምዕራብና በማዕከላዊ ኦሮሚያ በርካታ አካባቢዎች በአገዛዙ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸሙ ተመሣሣይ ግድያዎችን የሚያጋልጡ መረጃዎችም ከቅርብ ቀናት ወዲህ ወደ ህዝብ እይታ እየወጡ ይገኛሉ።

እነዚህን የጋምቤላና እና ሌሎች የኦሮሞ ጭፍጨፋዎችን አስመልክቶ የወጡ የዜና ዘገባዎችን ለመሸፋፈንና የህዝብን የትኩረት አቅጣጫ ለማስቀየር አገዛዙ በቶሌ ከባድ እልቂት በመፈፀምና በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት እንደተፈጸመ በማስመሰል መጮህና ጀሌዎቹንም ማስጮህ በማቀድ፣

2ኛ. “የምኒልክ ዘመቻ” እየተባለ በሚጠራው የአብይ አህመድ ፀረ ህዝብ ዘመቻ በወሎ አካባቢ የአገዛዙ ሰራዊት አባላት: ተባባሪ ሚሊሻዎችና የአገዛዙ አቀንቃኝ አርቲስቶች: ፖለቲከኞችና ሀብታሞች ሰላማዊ ዜጎችን በጠራራ ፀሀይ ከመኪና እያወረዱ በዘግናኝ ሁኔታ የጨፈጨፉበት ቪዲዮ ከሰኔ 17 ቀን 2022 ጀምሮ በመደበኛ ሚዲያዎችና በማህበራዊ ድህረ ገፆች በሰፊው ተሰራጭቷል። ወንጀሉ የተፈፀመው በዋናነት በመደበኛው የኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይሎች እና በፋኖ ሚሊሻዎች ሲሆን ወንጀሉ በተፈጸመበት ወቅት የፋኖ ሚሊሻዎች በአገዛዙ የጦር ዕዝ ቅንጅት ስር በነበሩበት ሰዐት መሆኑ የሚታወስ ነው:: በዚህ የዘር ማጥፋት እርምጃም ዋነኛው ተዋናይና ተጠያቂ መንግሥት ነኝ ባዩ የገዳዮች ቡድን መሆኑም በሁሉም አካላት አየተረጋገጠ መጥቷል። ይሄንንም አሰቃቂ በወሎ ኦሮሞዎች ላይ የተፈፀመን ጭፍጨፋ ዜናዎች ለመሸፋፈን: ለማረሳሳትና የአለምን የትኩረት አቅጣጫ ወደሌላ አሰቃቂ ግን በገለልተኛ አካል ለመዘገብ አስቸጋሪ የሆነ ጉዳይ ለማስቀየር የአብይ መንግስት አንድ የተለየ ድራማ ማዘጋጀት ነበረበት:: ይሄንንም ለማሳካት በቶሌ አካባቢ በሚኖሩ ንፁሀን ዜጎች ላይ ግፍ ወሰነ:: በውሳኔውም መሠረት በቶሌ ለፍተውና ግረው ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ኑሮ የሚኖሩ ሰላማዊ ዜጎችን
በመጨፍጨፍ በደቂቃዎች ልዩነት በሚቆጣጠራቸው መደበኛና ማህበራዊ ሚዲያዎቹ ላይ በመልቀቅ ወንጀልን በወንጀል ለማጣፋት ሞከረ:: በተወሰነ ደረጃም ተሳካለት:: የዚህን ሥርአት እኩይ ተግባር የሚያውቁና ራሳቸውም ሰለባ የሆኑ አንዳንድ አካላት ከኦነግ ስትራቴጂያዊ ግብ ካላቸው ጥላቻ ብቻ በመነሳት የመንግሥት ገደል ማሚቶ ሲሆኑ አይተን ታዝበናል::

3ኛ. የኢትዮጵያን የእርስ በርስ ጦርነት ለመፍታት ሁሉን አቀፍ የሰላም ሂደት በነፃ አካላት እንዲያዘጋጅ በአገዛዙ ላይ አለም አቀፍ ጫና መኖሩ ግልፅ ነው። በዚህ ነፃና ተአማኒ የሚባለው የፖለቲካ ውይይትና ድርድርም የብልጽግና ፓርቲ የኦሮሞን ህዝብ የሚወክል ብቸኛው ድምጽ በመሆን ለመታየት እና ሆኖም ለመቅረብን ይመኛል። ለዚህም ስኬት አገዛዙ ገለልተኛ በሆኑ አለም አቀፍ እና ሀገራዊ አካላት በሚዘጋጀው እና በሚመራው መድረክ ላይ የኦነግ – ኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ሥምና ቁመና እንዲበላሽና ሠራዊቱ የኦሮሞን ህዝብ የሚወክል ተአማኒ የፖለቲካ አካል ሆኖ እንዳይቀርብ፣ ቢቀርብም በተፈበረኩ ውንጀላዎች አንገቱን ያቀረቀረ ተሳታፊ እንዲሆን የቻለውን ሁሉ ድንጋይ ይፈነቅላል:: ለዚህም ይረዳው

ዘንድ አሁን በቶሌ ነዋሪዎች ላይ የሞት ድግስ ደገሰ:: ያለ ርህራሄም ፈፀመው:: ነገም በተመሣሣይ መልኩ የአያሌ ንፅሀንን ህይዎት እንደሚቀጥፍ መገመት አስቸጋሪ አይሆንም:: ይህ እኩይ ቡድን ያልገባው ነገር ቢኖር እኛ ለህዝባችን ነፃነት ክቡር ህይዎታችንን ለመስዋዕትነት ያቀረብነው ድልን በአቋራጭ መንገድ ከጠረጴዛ ላይ ልንወስድ አልመን ሳይሆን፣ በክንዳችን ጠላትን አንበርክከን ለማረጋገጥ እንደሆነ ያለንን ቁርጠኝነት እንገልፃለን:: ይህ ደግሞ በንፁሀን ደም በሚፈፀም የፖለቲካ ንግድ ሊስተጓጎል የማይችል መሆኑን ከፍ ባለ ድምፅ ልናሳስባችው እንፈልጋለን::

የቶሌን ጭፍጨፋ በሚመለከት የሚያሳዝነው ሌላው ጉዳይ በምዕራብ ኦሮሚያ የሚፈፀሙ ነገሮች ሁሉ ተአማኒ በሆኑ ሶስተኛ አካላት ማረጋገጥ ፈጽሞ እንይቻል መደረጉ ነው። አለም አቀፉ ማህበረሰብና ገለልተኛ አካላት አገዛዙ እየፈፀማቸው ያሉትን ግፎች እንዳይመረምሩና እውነታውን እንዳያውቁ ለማድረግ በማሰብ አካባቢውን ከሌላው አለም አቆራርጧል። ምንም አይነት የመገናኛ አውታሮች ሁሉ በአብዛኛው የምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ ተቋርጧል፣ በተወሰኑ ጥቂት ቦታዎችም ያሉት ይቆራረጣል:: በሌላ በኩል ደግሞ በአካል ተግኝተው ለመዘገብ የሚፈልጉትንም ቢሆን አካባቢው ለህይወት እንደሚያሰጋቸው በማስፈራራት እዚያ ቦታ እንዳይደርሱ አድርጓል:: ይሄንንም የአገዛዙ ቁንጮ አብይ አህመድ ወለጋ ለመሄድ ለህይወቱ እንደሚፈራ በአደባባይ በመግለፅ ፍርሀትን ለመዝራት መሞከሩ ይታወሳል:: በዚህም መሠረት ወንጀሉን ለመደበቅ አካባቢውን በጨለማ ውስጥ እንዲቆይ ያደረገ ቢሆንም እውነትን በፍፁማዊነት መደበቅ ስለማይቻል፣ ብዙ የአለም ማህበረሰብ አካላትና አባላት የብዙዎቹን ክስተቶች ፈፃሚና አስፈፃሚ በመረጃና ማስረጃ ሊያገኙት ይችላሉ። በኛ በኩል ግን በምዕራብ ኦሮሚያ በቅርቡ በቶሌ አካባቢ የተፈፀመው አሰቃቂ ወንጀል በገለልተኛ አካል እንዲጣራ በአፅንኦት እንጠይቃለን።

ከዚህ ቀደምም በሰጠናቸው ጋዜጣዊ መግለጫዎች ላይ በተደጋጋሚ እንደገለጽነው፣ ወንጀለኞች በህግ እንዲጠየቁ፣ ለተጎጂዎች ፍትህ እንዲሰጥ እና ለቤተሰባቸው በቂ ካሳ እንዲከፈል፣ እንዲሁም በዚህኛው ብቻ ሳይሆን ከዚህ ቀደም በተከሰቱት ግድያዎችና የጅምላ ጭፍጨፋዎችም ላይ ተዓማኒ የሆነ ገለልተኛ ምርመራ እንዲደረግ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

የኦሮሚያ ሰላም ለአፍሪካ ቀንድ ወሳኝ ነው!!
ድል ለኦሮሞ እና ለተጨቆኑ ህዝቦች በሙሉ!

የኦነግ-ኦነሠ ከፍተኛው ዕዝ
ሰኔ 20፣ 2022

Leave a Reply

Discover more from Qeerroo Bilisummaa Oromoo

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading