• Sun. Apr 26th, 2026

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አመራሮች እና የፖለቲካ ኦፊሰሮች ከእስር መፈታትን አስመልክቶ (የኦነግ – የኦነሰ ከፍተኛ አዛዥ መግለጫ)

Sep 6, 2024

ከአራት ዓመት በላይ በተለያዩ የብልፅግና እስር ቤቶች ውስጥ ስትሰቃዩ ቆይታችሁ በዛሬው ዕለት እንኳን ከቤተሰባችሁ እና ዘመዶቻችሁ ጋር በሰላም ለመገናኘት አበቃችሁ። የተወሰደው እርምጃ የትግሉ ውጤት ከመሆኑም በላይ፣ የኦሮሞ የነጻነት ትግል ተፋላሚው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የፈጠረው ተፅዕኖ መሆኑ አያጠያይቅም። በዚህ አጭር መግለጫ፣ የብልፅግናን ቡድን ፖለቲካዊ ዉሳኔ አንድምታን እና ይህንን እንዲወስን ያስገደዱትን ተጨማሪ ምክንያቶችን እንገልፃለን።

  1. ይህን የብልፅግና ፓርቲ ፖለቲካዊ ውሳኔ፦ “የኦነግ አመራሮችን ከእስር ፈታ” ብሎ ማስተጋባት ስህተት ነው። የፖለቲካ አመራሮቹ የእስር ገመድ ረዘመ እንጂ አሁንም በብልፅግና ቁጥጥር ስር ናቸው። እንደገና ሊታሰሩ ይችላሉ፣ ለደህንነታቸውም ምንም ዋስትና የለም። ከሁለት ዓመት በፊት ከእስር የተፈቱት የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ (ኦፌኮ) ፓርቲ አመራሮች ሐገር ውስጥ ለመኖር አልቻሉም። ጃል በቴ ኡርጌሳን “ከእስር ቤት አውጥተንሃል” ካሉት በኋላ በጥይት ደብድበው ገድለዉታል።
  2. እነዚህ የፖለቲካ መሪዎች ተይዘው የታሰሩት ወንጀል ፈፅመው ሳይሆን ፅኑ የፖለቲካ አቋም ስላላቸው ብቻ ነበር። የብልፅግናው ቡድን በእነርሱ እና አሁንም በሺዎች የሚቆጠሩ በእስር ቤት ውስጥ ባሉት ላይ ለፈፀመው እና ለሚፈፅመው ወንጀል ተጠያቂ ነው። ግዜውን ጠብቆ በህግም ሆነ በታሪክ ተጠያቂ ይሆናል።
  3. ከአራት አመት በፊት እነዚህ የፖለቲካ መሪዎች ሲታሰሩ፣ ኦነግ እና ኦፌኮ፣ በአጠቃላይ የኦሮሞ ፖለቲካ ማህበረሰብ በሰላማዊ መንገድ ብልፅግናን ሊወዳደር የሚችል ጠንካራ ኃይል በመገንባት ላይ ነበሩ። ይህም ጠንካራ ኃይል እውን እንዳይሆን ብልፅግና ብዙ ነገሮችን አበላሽቷል። ኦነግ አንድም ቢሮ ኖሮት እንዳይንቀሳቀስ በተጨማሪም መሪዎቹ እንዲዳከሙ ተደርጓል። ስለዚህም ይህ ውሳኔ፣ እነዚህን መሪዎች ማሰርም ሆነ አለማሰር በብልፅግና ላይ ምንም አይነት የፖለቲካ ተፅእኖ እንደማያደርሱ ግምት ውስጥ በማስገባት፣ በንቀት የተወሰደ ውሳኔ ነው። ውሳኔውም ምናልባት ምርጫ ቢደረግ (ለዛም ከደረስን) የብልፅግናን ተውኔት ከማጀብ ውጪ ተፅእኖ የማድረግ ችሎታ እንደሌላቸው በመቀመር የተደረገ ፖለቲካዊ ውሳኔ ነው።
  4. የብልፅግና ሰራዊት በውስጥም ሆነ በውጪ ኃይሎች ትልቅ ወጥመድ ውስጥ ገብቷል። ስለዚህም ውሳኔው፣ ለኦሮሞ ህዝብ “መሪዎችህን ፈትተንልሃል ከጎናችን ቁም” በሚል መልዕክት የኦሮሞ ወጣቶችን የጥይት እራት (የመድፍ መኖ) ለማድረግ የተተለመ ውሳኔ ነው። ይህም “ብልፅግና ከየኦነግ – የኦነሰ (OLA) ጋር እውነተኛ የእርቅ ድርድር ለማድረግ እንፈልጋለን” ከሚለው ድራማ ጋር ተመሳሳይ ነው።
  5. በመጨረሻም ይህንን ምክንያት በማድረግ ለብልፅግና ለማሸብሸብ የሚዳዳችሁ ሰዎች (የብልፅግና ካድሬንም ጨምሮ)፣ “ነገም ያለምንም ምክንያት እሰረኝ፣ ከእስር ስፈታ በዘፈን ምስጋናዬን አቀርብልሃለሁ” እያላችሁ እንደሆነ ልናስገነዝባችሁ እንወዳለን።

የኦሮሞ ነፃነት እውን የሚሆነው በልጆቹ ትግል ብቻ ነው።

የኦነግ – የኦነሰ ከፍተኛ ዕዝ

መስከረም 5፣ 2024

Leave a Reply

Discover more from Qeerroo Bilisummaa Oromoo

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading