• Sun. Feb 15th, 2026

የቶሌን ጭፍጨፋ በሚመለከት አስቸኳይ ገለልተኛ የሰብአዊ መብት ጥበቃ አካላት ምርመራ እንዲደረግ ስለመጠየቅ – ከኦነግ-ኦነሠ የተሰጠ መግለጫ

Jun 22, 2022

የቶሌን ጭፍጨፋ በሚመለከት አስቸኳይ ገለልተኛ የሰብአዊ መብት ጥበቃ አካላት ምርመራ እንዲደረግ ስለመጠየቅ

ከኦነግ-ኦነሠ የተሰጠ መግለጫ

በቶሌ መንደር በቅርቡ የተፈፀመውን ጭፍጨፋ በሚመለከት በአገዛዙ የተለያዩ አካላትና በመገናኛ ብዙሀኑ አማካይነት በኦነግ-ኦነሠ ላይ የተሰነዘሩ በርካታ የውሸት ወሬዎች ሲሰራጩ እየተመለከትን ነው። ይህ ውንጀላ እስካልታረመ ድረስ ደግሞ ለጥፋቱ የህግ ተጠያቂነትንና ለተጎጂዎች ፍትህን ማግኘት ከባድና አስቸጋሪ ይሆናል። እነዚህ ወደ ኦነግ-ኦነሠ እየተቀሰሩ ያሉትን ጣቶችንና ውንጀላዎች በተመለከተ ግልጽ መሆን የሚገባቸው ጠቃሚ ነጥቦችን በዚህ መግለጫ ማቅረብ አስፈላጊ ሆኗል።

የኦነግ-ኦነሠ በቅርቡ በጊምቢ ያካሄደውን ወደራዊ እርምጃ ከዚህ እልቂት ጋር ለማያያዝም በብዙዎች ተሞክሯል። እውነቱ ግን በጊምቢ የተካሄደው ኦፕሬሽን ማክሰኞ ሰኔ 14 ቀን የተካሄደ ሲሆን የዚህ ኦፕሬሽን አላማ የፖለቲካ እስረኞችን ነፃ ማውጣት፣የመሳሪያ ዲፖዎችን መያዝ እና የአገዛዙን የጦር ሀይል በመምታት የጦርነት አቅሙን ማዳከም ብቻ ነበር። ለዚህም የተለያዩ የፖለቲካ እስረኞች የታጎሩበት እስር ቤት እና ሁለት ወታደራዊ ካምፖች ላይ ኢላማ ያደረገ ነበር። አንደኛው የመከላከያ ጦር ካምፕ ሆኖ የሚያገለግል ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ለኦሮሚያ ክልል “ጋቻና ሲርና” (የሥርአት ጋሻ) የሚባሉ ሚሊሻዎች ካምፕ ሆኖ ያገለግላል። እነዚህ ሁለቱም ኢላማዎች በከተማው ውስጥ የሚገኙ ናቸው:: አንድ ቀን የፈጀውን ይሄን ውጊያ ተከትሎ የተሸነፉ እና በህይዎት የተረፉት የአገዛዙ ወታደሮች ከሁለቱም ግቢዎች አምልጠው ማምሻውን ከከተማው ሸሽተው የወጡ ሲሆን እነዚህ ኃይሎች ወደ ነቀምት በሚወስደው A4 አውራ ጎዳና ወደ ምዕራብ እንዳመለጡም አውቀናል። በነጋታው እሮብ (ሰኔ 15 ቀን 2022) ጥዋት ላይም የእኛ ሃይሎች የተማረከውን መሳሪያ ይዘውና እስረኞችን ነፃ አውጥተው ከጊምቢ ከተማ ለቀው የወጡ ሲሆን ይሄንንም በኦፕሬሽኑ ወቅት እና በኋላም በተለያዩ የዜና ማሰራጫዎች መዘገቡ ይታወሳል። ይህ በአባሴና፣ ቶሌ እና አካባቢው በሚገኙ መንደሮች ላይ የተፈጸመው እልቂት ግን ይህ ኦፕሬሽን ከተጠናቀቀ ከ3 ቀናት በኋላ ነበር። ይህንን ጉዳይ የበለጠ ለመረዳት የሚከተሉትን ነጥቦች በአንክሮ ማጤን ያስፈልጋል:-

1ኛ. ጭፍጨፋው በተፈጸመበት ቀን በጊምቢ እና በነቀምት መካከል ያለው A4 አውራ ጎዳና ሙሉ በሙሉ በስርዓቱ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ነበር። ሁለቱን ከተሞች የሚያገናኘውን ይሄን መንገድም ለማንኛውም መጓጓዣ ዘግተውት የነበረ ሲሆን ጭፍጨፋው የተፈፀመበት ቦታ በእነዚህ ሁለት ከተሞች መካከል ባለው A4 አውራ ጎዳና ላይ ከጊምቢ 50 ኪ.ሜ እና ከነቀምቴ 63 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኝ ነው። በዚህ ጊዜና ቦታ የአገዛዙ ኃይሎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጭፍጨፋ እንዲፈጽሙ ያስገደዳቸው ወታደራዊም ይሁን ስነልቦናዊ ጫና ምን እንደነበረ ግልጽ የሆነ መልስ ባይኖረንም በሌሎች አካባቢዎች የአገዛዙ ኃይሎች ወታደራዊ ሽንፈት ሲያጋጥማቸው ሲቪል ማህበረሰቦችን የበቀል ዒላማ እንደሚያደርጉ ግን ብዙ ጊዜ አይተናል:: ለህዝብም በተደጋጋሚ ገልፀናል:: ከነበረን ልምድና ከጠላት የወረደ የሞራል ደረጃ ተነስተን የዚህ አይነት የብቀላ እርምጃ የሆነ ቦታ ላይ በሆነ ጊዜ ሊፈፀም እንደሚችል ገምተን የነበረ ቢሆንም አንዳችም ወታደራዊ ግጭት ባልነበረበት በዚህ አካባቢ ያደርጉታል ብለን ግን ፍፁም አልጠበቅንም:: በእርግጠኝነት የሚታወቀው ግን ሰኔ 20፣ 2022 ቀን፣ ጭፍጨፋው ተፈፀመ በተባለበት ዕለት የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት በቦታው ብቻ ሳይሆን በአካባቢውም ያልነበረ መሆኑን ነው።

2ኛ. በኛ ማጣራት ከሚዲያው ዘገባ በተቃራኒ ከወሎ በመጡ ሰፋሪ አማርኛ ተናጋሪዎች ብቻ ሳይሆን አያሌ የኦሮሞ ተወላጆችም በጅምላ ጭፍጨፋው እንደተገደሉ አረጋግጠናል። እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ አንዳንድ አለምአቀፍ ሚዲያዎችን ጨምሮ ብዙ አካላት ይህን መሠረተ ቢስ ውንጀላ የአገዛዙ ባለስልጣናት የሰጡትን የተቀናጁ መግለጫዎች እና ያልተረጋገጡ ወሬዎች ተቀብለው ማናፈሳቸው አሳዝኖናል:: የነዚህ ውንጀላዎች ብቸኛው ማስረጃ ደግሞ ወንጀለኞቹ አፋን ኦሮሞ ተናጋሪዎች የነበሩ መሆናቸውን ምስክር የተባሉት ሰዎች መግለፃቸው ብቻ መሆኑ አስተዛዛቢ ሆኗል:: በአገዛዙ ወታደራዊ ሀይሎች ውስጥ በተለይም በኦሮሚያ ልዩ ሀይልና ሚሊሻ ውስጥ አብዛኛዎቹ አፋን ኦሮሞ ተናጋሪዎች እንደሆኑ እነዚህ አካላት አያውቁም ብለን ግን አናምንም ። ስለሆነም ሚዲያዎች በሁኔታው በቂ መረጃ እና ማስረጃ ሳይኖራቸው የፋሺስቱን ቡድን ጥቅምና ትልም ብቻ ባማከለ መልኩ ሁኔታውን ማዛባታቸው በጨፍጫፊው የአብይ መንግሥት ወጥመድ ውስጥ ፈቅደው መውደቃቸውን ያሳያል። ገዥው አካል ይህን የመሰለ የጭካኔ እቅድ ሲነድፍም ሆነ ሲፈፅም ያለውን የሚዲያ ሞኖፖሊና ውሸት የማሰራጨት ችሎውን በመተማመንና በኦሮሚያ እየፈፀመ ያለውንም ግፍ ሀቀኛ ለማስመሰል አቅዶ እንደሆነ የታወቀ ሲሆን ይህ ለጊዜው በተወሰነ መልኩ የተሳካለትም ይመስላል። ከዚህም በላይ ይህ ያልተረጋገጠ ዘገባ አገዛዙን ለጊዜውም ቢሆን ከተጠያቂነት እንዲያመልጥ ምቹ ሁኔታ ስለሚፈጥርለት በአስቸኳይ መታረም አለበት።

3ኛ. ይህ አሰቃቂ ድርጊት አገዛዙ የኢንተርኔት እና የስልክ አገልግሎትን በመዝጋት የመረጃ ፍሰት ላይ ሙሉ ቁጥጥር (ሞኖፖሊ) በያዘበት አካባቢ የተፈፀመ ነው። ይህም የዚህ ጭፍጨፋ ዜና ወዲያው እንዳይታረም እና ኦነግ-ኦነሠ በአማራ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ፈፀመ የሚለውን የተቀነባበረ የውሸት ዜና በሰፊው እንዲናፈስ አስችሏል። ይህ የመሰሪዎች ቡድን፣ በተወሰነች አካባቢና ለተወሰኑ የተመረጡ የአካባቢው ሰዎችም ኔትወርክ በመፍቀድ የተቀነባበሩና የተመረጡ የውሸት መረጃዎችም ሲወጡ አይተን ታዝበናል:: ከዚህ በፊት በምዕራብ ኦሮሚያ የሚከሰቱትን ድርጊቶች መዘገብ ወይም ማጣራት እንደማይችል ገልፆ የነበረው የአገዛዙ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እንኳን በአካባቢው በየጊዜው የሚፈጸሙ ሌሎች የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ሰምቶ እንዳልሰማ ሲያልፋቸው የነበረ ቢሆንም፣ በዚህ ጉዳይ ግን በቅፅበት የአገዛዙን ትርክት የሚያጠናክር ዘገባ አቅርቧል። እንደለመደውም ሁሉ ኢሰመኮ ይህንን ዘገባ ያቀረበው ጭፍጨፋው ከተፈፀመ 24 ሰአት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እና አንዳችም መሠረታዊ የሆነ ምርመራ ከማድረጉም በፊት ነው።

ጥልቅ ምርመራ ቢያደርግ ኖሮ ኢሰመኮ ቢያንስ ከተጎጂዎች መሀከል ግማሾቹ ኦሮሞዎች መሆናቸውን ማወቅ በቻለ ነበር። ከዚህ በፊት በጉሊሶ፣ በባቦ ጋምቤል እና በሌሎችም አካባቢዎች በአገዛዙ ኃይሎች እና አጋሮቹ በሰላማዊ ሰዎች ላይ አሰቃቂ ጥቃቶች ሲፈጸሙ ያየነውም የኢሰመኮን ተመሳሳይ አሰራር ነበር። በተለይም የጉሊሶን እልቂት በተመለከተ አገዛዙ ጣቶቹን ከ1000 ኪሎ ሜትር ርቀት በላይ ወደሚገኘው የትግራይ መንግስት ሳይቀር በመቀሰርና ጭፍጨፋውንም እንደ አንድ ምክንያት ተጠቅሞ ከ2 ቀናት በኋላ በትግራይ ላይ ወታደራዊ ጥቃት ከፍቷል። የሚገርመው ግን እነዚህ መጠነ ሰፊ ጭፍጨፋዎች የአብይ ፋሺስታዊ ቡድን ከትግራይ መንግሥት ጋር ጦርነት ላይ በነበረበት ወቅት መቆማቸው ነው::

4. ሌላው ቁም ነገር ደግሞ እስካሁን ተአማኒነታቸው ያልተረጋገጡ ሁለት በስልክ ተናገሩ የተባሉት ምስክሮች ውጪ ከ300 ሰዎች በላይ ተገድለውበታል የተባለበትን አሰቃቂ ድርጊት በተመለከተ የትኛውም ገለልተኛ ሚዲያ እውነተኛ ማስረጃ ለማግኘት ጥረት አለማድረጋቸው አሳሳቢ ሆኖ አግኝተነዋል።

5. የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ምን አይነት ተሳትፎ እንደነበረው የሚያሳዩ ምንም አይነት ማስረጃዎች በሌሉበት፣ በሚያሳዝን ሁኔታ የተከበረ የጋዜጠኝነት ስነ-ምግባር ያላቸው ጋዜጠኞች እና ታዋቂ የዜና አውታሮች ስለ ጭካኔው አውቀውም ይሁን ሳያውቁ የተዛባ ሪፖርት ሲያደረጉ እና አለምን ሲያሳስቱ ስናይ ተአማኒነታቸውን ጥያቄ ውስጥ እንድናስገባ የተገደድን ሲሆን፣ እነሱም የክስረት አደጋ ውስጥ መሆናቸውን አይተናል። እንዲህ ዓይነቱ ትክክለኛ ያልሆነ ዘገባም በክልሉ ውስጥ የሚከሰቱ ግጭቶችን ለመፍታት አስተዋፅኦ ያደርጋል ብለን በፍፁም አናምንም:: ይልቁንም ቀድሞውንም ለግጭት ተጋላጭ በሆነው ክልል ውስጥ ሰፊ ማህበሰባዊ ግጭትን ይፈጥራል ብለን እንሰጋለን።

እንደዚህ አይነት አስጸያፊ ድርጊቶች በኢትዮፕጵያ እየተለመዱ የመጡ ሲሆን እውነትነታቸው በፖለቲካ ቁማርተኞች እየተዛባ ህብረተሰቡን ማሳሳቱ እየተለመደ መጥቷል። የረጅም ጊዜ የህዝቦች የፍትህ ጥያቄም በመሠረተ ቢስና ግትልትል ውንጀላዎች ለማደናቀፍ ታቅዶ ተቀናጅቶ እየተሰራበት እንደሆነ ይታወቃል። ለዚህም ነው እኛ የገለልተኛ አካላት ምርመራ ጥሪ ለድርድር የማይቀርብ ጉዳይ መሆኑን ደጋግመን የገለፅነው። አለምአቀፍ የሰብአዊ መብት ተቋማትና ገለልተኛ አካላት ገብተው እነዚህን እኩይ ድርጊቶች ያለምንም እንቅፋት ሙሉ ምርመራ እስኪያደርጉ ድረስም፣ ለተጎጂዎች ማንኛውንም አይነት ፍትህ ለማምጣት ማሰብ ወይም ከገዥው አካል ፍትህን መጠበቅ ከንቱ ልፋት ነው። ይህን የመሰሉ እና ሌሎችንም በሀገሪቱ ውስጥ ቢያንስ በቅርብ አመታት በህዝብ ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎችን በተመለከተ በአስቸኳይ አለም አቀፍ አጣሪ ቡድን እንዲረምረው ደግመን ደጋግመን እንጠይቃለን።

ፍትህ ለተጎጂዎች!!

የኦነግ – ኦነሠ ከፍተኛው ዕዝ ሰኔ 22, 2022

Leave a Reply

Discover more from Qeerroo Bilisummaa Oromoo

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading