ሚያዚያ 13/2024 አራታ ቢዮሌሳ ኦሮሚያ (ONM-ABO)
ጃል በቴ ኡርጌሳ ቡላ በምስራቅ ሸዋ ዞን፣ ዱግዳ ወረዳ፣ በቀሌ ጊሪሳ ቀበሌ ውስጥ ከአባታቸው ኦቦ ኡርጊ (ኡርጌሳ) ቡላ እና ከእናታቸው አዴጎደኖ ቦባ በ1978 ተወለዱ። ጃል በቴ በዚሁ በበቀሌ ጊሪሳ ቀበሌ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ከ1988-1991 ተከታትለው ከዚያም ከ5-8 ክፍል ትምህርታቸውን በመቂ መካከለኛ ትምህርት ቤት አጠናቀቁ። ከዚህ በመቀጠል ከ1992 እስከ 1995 ሁለተኛ ደረጃ ከ9-12 ክፍል ትምህርታቸውን በመቂ ካቶሊክ ትምህርት ቤት፣ ከዚያም ከፍተኛ የትምህርት ውጤት 3.6 በማምጣት ከ1995-1998 በባህርዳር ዩንቨሪሲቲ በመምህርነት ሙያ ሰለጠኑ።
ጃል በቴ የመምህርነት ሙያቸዉንም በባዮሎጂ ከ1999-2005 ከተማሩና ከተመረቁ በኃላ በዶቦንሶኮ ባቱ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመምህርነት ተመድበው ሰርተዋል። የአራምቤ ኮሌጅ አስተዳዳሪ እንዲሁም ለአዳማ ቅድስት ማሪያም ኮሌጅ የርቀት ትምህርት ዋና አስተባባሪ በመሆንም አገልግለዋል። በመቀጠልም በነቀምቴ ኪያ ሜዲ የጤና ኮሌጅ በአስተዳዳሪነት እየሰሩ ለትምህርት ባላቸው ፍላጎት የተነሳ የጤና መኮንንነት ትምህርት ተምረው በከፍተኛ ውጤት ተመርቀዋል። በተጨማሪም ነቀምቴ በሚገኘው የወለጋ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ የመጀመሪያ ዲግሪ ቀጥሎም በአግሮ ኢኮኖሚክስ ትምህርት የሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል።
ጃል በቴ በማንነታቸው ማለትም በኦሮምነታቸው ምክንያት ባገለገሉባቸው ቦታዎች ሁሉ ለሚደርስባቸው ተፅዕኖ አንገታቸውን ደፍተው ኑሮዬ ነው ብለው በዝምታ የማያልፉ ሲሆን፣ ከውጪም ሆነ ከዉስጥ ለሚደርስባቸው ጫና እጃቸውን ሰጥተው አያውቁም።
የኦሮሞ ህዝብ ነፃነት ጉዳይን በተመለከተም በጣም ጠንካራ አቁዋም ስለነበራቸው ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ስለ ኦሮሞ ሕዝብ ነፃነት ትግል ሳይግልፁ አያልፉም ነበር። በዚህም አቋማቸው በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቆይታቸው ጊዜ ለኦሮሞ የነፃነት ትግል ተማሪዎችን ሲያደራጁ ቆይተዋል። ባህርዳር ዩንቨሪሲቲ በነበሩበት ጊዜም የኦሮሞ ተማሪዎችን በማደራጀት ከፍተኛ ሚና እና ዉጤት በማስገኘታቸውም ታሪክ ይዘክራቸዋል። በዚህም አቋማቸው በእስራትም ተቀጥተዋል።
ጃል በቴ በ2010 ትዳራቸውን የመሰረቱ ሲሆን የአራት ልጆች፤ የአንድ ወንድ እና የሶስት ሴቶች አባት ነበሩ።
በኦሮሞ ነፃነት ትግል ውስጥ የላቀ ተሳትፎ የነበራቸው ሲሆን በተለይም ህዝብን በማደራጀት ላይ አኩሪ ዉጤት አበርክተዋል። ለኦሮሞ ነፃነት ግንባር ሕዝብን የማደራጀት ስራ የጀመሩት በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበሩበትም ጊዜ ነበር። በ2005 በምስራቅ ሸዋ ዞን የኦሮሞ ነፃነት ግንባር አደረጃጀትን በማቀናጀት ውስጥም ከፍተኛ ድርሻ ነበራቸው። ክፉዋ ኢምፖየር ጭካኔዋን እያበረታች ብትሄድም የጃል በቴን ፅኑ የነፃነት እንቅስቃሴ ልትገታ አልቻለችም። በ2010 የኢምፖየሪቷ ሀገራዊ ምርጫ ላይ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስን ወክለው በዱግዳ ወረዳ ለፓርላማ ተወዳድረው ነበር።
ጃል በቴ የማያወላውል አቋም ያላቸው ታጋይ ስለነበሩም በኦሮሞ ወጣቶች (ቄሮ) እንቅስቃሴ ውስጥ በግምባር ቀደም መሪነት ሰልፍ ሲያቀናጁ ነበር። በወያኔ ዘመንም የኦሮሞ ወጣቶችን በምሳሌነት የመሩ ጠንካራ መሪ ስለነበሩ የወያኔ ተላላኪዎች አሰቃቂ ድብደባና የአጥንት ስብራትም ቢያደርስባቸውም ስነ፡ልቦናቸውን ግን መስበር አልቻሉም። እንቁው የኦሮሞ ነፃነት ታጋይ ጃል በቴ ዉድ ህይወታቸውን በጀግንነት ለኦሮሞ ህዝብ አሳልፈው የሰጡ ጓድ ናቸው።
ጃል በቴ ኡርጌሳ የጠላት ጥይት ሰውነታቸውን እና ግንባራቸውን እስከመታቸው እለት ድረስ ለኦሮሞ ህዝብ የገቡትን የታማኝነት ቃል አልሸራረፉም ወይም አልለወጡም፤ ለገቡት ቃል/አደራ በጥንካሬ ቆመው መራርዋን የሞት ጽዋ በክብር መሰዋእትነት መቅመሱን መረጡ።
ጃል በቴ ኡርጌሳ ሚያዚያ 9/2024 በመቂ ከተማ ካረፉበት ሆቴል ሌሊት ይዘዋቸው ግሪሳ ማዞሪያ በተባለበት ቦታ በስድስት ጥይት ጭንቅላታቸው እና ወገባቸው ላይ በማዝነብ ከገደሉዋቸው በኃላ ሜዳ ላይ ጥለዋቸው የሄዱ ሲሆን በማግስቱ ሚያዚያ 10/2024 አስከሬናቸው ተገኘ።
የጀግናችን ጉማ እና ሂሳቡም ይወራረዳል፤ እሳቸውም የተሰዉለት ዓላማ ከግብ ይደርሳል!
