በአሁኑ ግዜ ሰላማዊ ሰዎችን አግቶ ገንዘብ መጠየቅ፣ ከፍተኛ የማህበረ-ፖለቲካዊ እና የደህንነት ችግር በመሆን፣ በመላ ሃገሪቱ የብዙ ሰላማዊ ሰዎችን ህይወት እያዛባ ይገኛል። የዚህ ውስብስብ ወንጀል መንሰኤ፤ በህገወጥ መንገድ ገንዘብ ማግኘት፣ የፖለቲካ ብልሹነት እና የድህንነት መዋቅር መኮላሸት ናችው።
በምድር ላይ ያለውን እዉነታ ግልፅ ለማድረግ፤ የዚህ ድርጊት ተዋናዮች፣ መዋቅር እና ለዚህ እኩይ ተግባር ያነሰሳቸዉን ጉዳይ መረዳት አስፈላጊ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ፣ የገዢው ስራዓት የሆኑት የብልፅግና ፓርቲ አመራሮች፣ ሰላማዊ ሰዎችን በማገት ገንዘብ መጠየቅን ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የመወንጀያ መሳሪያ አድርግው እየተጠቀሙበት ይገኛሉ። ይህም ድርጊት የሚወጠነው ኮሬ ነጌኛ በሚባለው በኦሮሚያ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ደረጃ ሲሆን፣ በመላው ኦሮሚያ የሚተገብረዉም በሽመልስ አብዲሳ የሚመራው የዘራፊ እና ገዳይ ቡድን ነው። አብዛኛውን ግዜ፣ የእንደዚህ አይነት ድርጊት በሰላማዊ ማህበረሰብ ላይ ያለው ተፅእኖ ከፖለቲካ ግብ በኋላ የሚታይ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ምግብ መከልከል እና ሰው ሰራሽ ረሃብን የጦርነት ስልት በማድርግ ለፖሊቲካ ግብ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ። በሌሎች ሃገራት መንግስት ያልሆኑ አካላት እንደዚህ ባለ የማገት ተግባር የሚሳተፉት፣ መንግስት የህዝቡን ደህንነት ለመጠበቅ ያለውን የአቅም ማነስ ለማሳየት ነው። በኢትዮጵያ ግን ይህ ድርጊት ሙሉ በሙሉ የተገላቢጦሽ ሆኗል። መንግስት የህዝቡን ደህንነት ለመጠበቅ ያለው አቅም አናሳ መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር በሆነበት ግዜ፣ የመንግስትን አናሳ አቅም ለማሳየት አልሞ ሰላማዊ ሰዎችን ማገት የሚፈልግ አካል አይኖርም። ስለሆነም፣ መንግስት ተብዬው የራሱን ዜጎች የማገት ተግባር ላይ ተሰማርቶ የተቀናቃኞቹን ስም ለማጠልሸት ሲጥር ይታያል። የዚህ የመደበኛ ሚና መገለባበጥ የብልፅግናን እኩይ ተግባር በሌሎች ሃይሎች ላይ ለማላከክ የተሸረበ ሴራ ነው።
በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ተዋናዮች ደግሞ በየአካባቢው የሚገኙ የብልፅግና ካድሬዎች፣ ሰላዮች እና የእገታ ገንዘብ ማካበትን የሚያስተባብሩ የደህነት ኃይላት ናቸው። በዚህ ደረጃ ያሉት የኢኮኖሚ ጥቅም አሳዳጆች በዋናነት የሚያሳትፍ ሲሆን፣ እገታውን የሚያካሂዱት በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ያሉ ካድሬዎች እና የመንግስት ደህንነት መኮንኖች ናቸው። የላይኛው የፖሊቲካ አመራርም ይህ ወንጀል መሰራቱን እያወቀ፣ የተቃዋሚዎቹን ስም እስካጎደፈለት ድረስ አይቶ እንዳላየ እያለፈው ይገኛል። በቅርብ ግዜ በሰሜን ሸዋ፣ ገብረ ጉራቻ አካባቢ ላይ በተፈፀመው እገታ የክልሉ መንግስት ያልተቀናጀ የደመ-ነፍስ መልስ የሚያሳየው ይህ እገታ የተቀናጀው በመንግስት የደህንነት መኮንኖች እና በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ባሉ ካድሬዎቹ መሆኑን ያመላክታል። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ስለ እገታው ምላሽ የሰጠው በፊንፊኔ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በእገታው ላይ ሃሳብ ከሰጠ በኋላ መሆኑ፣ የአሜሪካ ኤምባሲ ሃሳብ ባይሰጥ ኖሮ የክልሉ መንግስት በቸልተኝነት ያልፈው እንደነበር ያሳያል። በኢትዮጵያ ወንጀሎችን እና ወንጀለኞችን በቸልታ ማለፍ ለረጅም ግዜ የተለመደ ባህል ሆኖ ቆይቷል።
በሶስተኛ ደረጃ በእገታ እና ዘረፋ ላይ የተሰማሩት ደግሞ መንግስት የረሳቸው ጥቂት ስራ አጥ እና ተስፋ የቆረጡ ወጣቶች ናቸው። የአራት ኪሎው የመንግስት ባለስልጣኖች በእርስ-በርስ ጦርነት እና ቅንጡ የከተማ ፕሮጀክቶች ተጠምደው ባሉበት ወቅት፣ ለዘረፋ የተደራጀው የወጣት ቡድን በሃገሪቱ ህግ እና ስርአት ማስከበር እንደሌለ በመገንዝብ፣ ዘረፋ ላይ መሰማራት ያለው አደጋ በዘረፋ ከሚያገኘው የገንዘብ ምንጭ ጋር አነፃፅሮ ገቢዉን ምርጫው ያደረገ ይመስላል።
ለእንደዚህ ዓይነት የስርዓት ችግር መፍትሄውም የስርዓት ለዉጥ ማምጣት መሆን አለበት። በጦርነት እና ቅንጡ ፕሮጀክቶች የተጠመደው ስርዓት፣ የፖለቲካ ተቃዋሚዎችን ለማጥፋት የደህንነት አካላቱን በመላው ሃገሪቱ አሰራጭቶ ያለ በመሆኑ፣ ገዢው ፓርቲ ህግ እና ስረዓትን የማስከበር ችሎታው ተኮላሽቷል። ሃገሪቱን እያስተዳደርኩ ነው የሚለዉ የመንግስት አካልም፣ ስር የሰደደ ስራዓታዊ ችግር መኖሩን ተቀብሎ፣ የፖለቲካ እና ደህነነት ችግር መኖሩን በማመን፣ ተቃዋሚዎችን እጅ ለማሰጠት ሲል ብቻ የሰላም ጥሪ ከማቅረብ ይልቅ ስር ነቀል የሆነ ስርዓታዊ መፍትሄ ለመሻት ቁርጠኝነቱን ማሳየት አለበት።
የኦነግ – የኦነሰ ከፍተኛ አዛዥ
ሐምሌ 11፣ 2024
