• Thu. Mar 12th, 2026

የኦሮሞ ፓርቲዎች የጥፋት ተባባሪነትን እምቢ ማለት አለባቸው፣ የኦሮሞ ባህል ከጭቆና መዳፍ ሊወጣና ሊጠበቅ ይገባል! (የኦነግ-ኦነሠ ጋዜጣዊ መግለጫ)

Feb 17, 2025

ከሞላ ጎደል ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ጋር በመላ አገሪቱ ውስጥ ግጭት የገባው የአብይ አህመድ አገዛዝ በኦሮሚያ ተስፋ የመቁረጥ እርምጃዎችን እየወሰደ ነው። አገዛዙ ባሳለፍነው ዓመት ብቻ የኦሮሞን ህዝብ ለማንበርከክ የተለያዩ የጭቆና ስልቶችን ነድፎ የተገበረ ሲሆን እነዚህ ስልቶች በሙሉ በሚያስደንቅ ሁኔታ ያልተሳኩ መሆናቸው ይታወቃል። ጦርነትን ሰላም አስመስሎ ህዝቡን የማደናገሪያ ኦርዌሊያዊ ዲስኩሩን ቢያሰራጭም ቅሉ አልተሳካም። ይባስ ብሎ በአሰቃቂው የደራ (ሰላሌ) ድርጊቱ የአማራና ኦሮሞን ህዝቦች ግጭት ለማባባስና እልቂት መፍጠር ሞክሮ ከሽፎበታል። በአርሲ አከባቢም የሀይማኖት ክፍፍል ግጭት ለመፍጠር ሞክሮ ከሽፎበታል። (አገዛዙ ይህንን አጀንዳ አሁንም በሌሎች አካባቢዎች በተለይም በጅማ ዞን እየገፋበት ነው)

አገዛዙ በኦሮሚያ ውስጥ ህዝብን በሰበሰበ ቁጥር ራሱን “የኦሮሞ መንግስት” ብሎ ቢያቀርብም፣ የቱንም ያህል ብሄርተኛ መስሎ የኦሮሞን ህዝብ ትኩረት ለመሳብ ቢሞክርም፣ ይህ ግን በህዝባችን ላይ የፈፀመውን ግፍ ሊሽርለት አልቻለም። በጥቂት የተባረሩ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት አባላት ዙሪያ የራሱ “ሸኔ” ተዋጊዎቹን ቡድን አሰባስቦ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አንጃ/ክፋይ እጅ እንደሰጠ አድርጎ ያቀረበው የፈጠራ ትርክትም አልተሳካም። ይህንን ትርክቱን ለማረጋገጥ በማዕከላዊ ኦሮሚያ ያለውን የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት እንቅስቃሴ ለማጥፋት ቢሞክርም በሚያስደንቅ ሁኔታ ከሽፎበታል። አሉ የተባሉ የኦፕሬሽን ስልቶች በሙሉ አሟጦ በመጠቀም በምዕራቡ የሠራዊታችን እዝ ላይ ዘምቶ የሚችለውን ቢሞክርም – አልተሳካም።  በሠራዊታችን ደቡብ እዝ ላይ በተከፈተው ዘመቻ ኬንያን እስከማሳተፍ ያደረገው ሙከራም አልተሳካም።

አሁን ደግሞ ገዥው ቡድን ሁለት አስከፊ እርምጃዎችን በልዩ ሁኔታ እየወሰደ ይገኛል። እነሱም:-

 1. የኦሮሞ ፓርቲዎችን በመጠቀም እየሞተ ያለውን ገፅታውን መልሶ ለማንሰራራት፡ የማህበራዊ መሠረት እጦት ቀውስ

ቀደም ብሎም ጉልህ ድጋፍ ያለው መስሎ ለነበረ፣ ነገር ግን በተገላቢጦሽ ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ጋር በሚባል ደረጃ ግጭት ውስጥ ለገባ መሪ፣ ቆም ብሎ አንድ መሰረታዊ ጥያቄ መጠየቅ ተገቢ ነው:- በውኑ አብይ አህመድ በእውነት ከጅምሩ የራሱ የሆነ ማህበራዊ መሠረት ነበረው ወይ?  አቢይ አህመድ ገና ከጅምሩ ሰፊ ድጋፍ ቢደረግለትም ትክክለኛ የፖለቲካ ማህበራዊ መሠረት እንዳልነበረው በኛ በኩል ግልፅ ነው።  በኢትዮጵያ ውስጥ እውነተኛ ህዝባዊ ማህበራዊ መሠረት ለመገንባት ቢያንስ:-

(ሀ) የህዝቡን ዋና ዋና ጥያቄዎችን የሚፈታ በሚገባ የተደራጀ ሀሳብ እና

(ለ) ለነዚህ እሳቤዎች የትግል እና የመስዋዕትነት ታሪክ መኖሩ የግድ አስፈላጊ ነው። 

አብይ አህመድ ከእነዚህ ውስጥ አንዱንም የለውም። (ሀ) በብዙሃኑ የትግል ጥያቄ ላይ የተመሰረተ በገሃዱ ዓለም የሚታይ ወጥ የሆነ እይታ ወይም መርሆ የለውም።  በከንቱ ብልጭልጭ ፕሮጄክቶች ላይ ያተኮረው – ማለትም እንደ መዝናኛ ፓርኮች እና የመንገድ ዳር መብራቶች ያሉትን በመገንባት መጠመዱ እንዲሁም በትውልዶች ትጋት የተገነቡ የሺዎች ቤተሰብ ቤቶችን ያለ ምንም ካሳ ማፍረሱ፣ አገዛዙ ከህዝቡ ምኞቶች እና እውነተኛ ፍላጎቶች በፍጹም የተፋታ ስለመሆኑ ጥቂቶቹ ማሳያዎች ናቸው። (ለ) በማይገርም ሁኔታ ለህዝባችን ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ፍላጎቶች ትርጉም ያለው ትግል እና መስዋዕትነት ታሪክ የለውም። የአብይ አህመድ ታሪክ ከጅምሩ የትምህርት ማስረጃን ጭምር በማጭበርበር ወደ ስልጣን ተጠግቶ የህዝባችንን ፍትሃዊ ትግል ለማኮላሸት መንደፋደፍ ነው።

የአብይ አህመድ  “ለውጡ” በተባለው በመጀመሪያዎቹ ጊዜያት ያገኘው ድጋፍ ከሁለት ምንጮች የመጣ ነበር።

  1. በወቅቱ ከኢህአዴግ ውጪ የተደራጀ አማራጭ ሀይል ባለመኖሩ እራሱን የንቅናቄው መሪ አድርጎ በማቅረብ የኦሮሞን አብዮት አስታኮ ሂደቱን እንዲጋልብ ስለ ተፈቀደለት እና
  • የራሳቸው ማህበራዊ መሠረት የነበራቸው ሌሎች ፓርቲዎች እና ግለሰቦች፣ ድጋፋቸውን በጓሮ ድርድር፣ በደጋፊነትና በአንዳንድ አጋጣሚዎች ሀገራቸውን ለመለወጥ ባላቸው እውነተኛ ግን የተሳሳተ እምነት ደጋፊዎች ድጋፋቸውን ወይም ይሁንታቸውን ለዓብይ በማሳየታቸው በተዘዋዋሪ መንገድ ያገኘው ድጋፍ ነው።

ስለዚህ፣ ድጋፍ መስሎ ይታይ የነበረው፣ በእውነቱ፣ ጊዜያዊ አሰላለፍ እንጂ በመተማመን፣ በጋራ ዓላማ ወይም በመስዋዕትነት ላይ የተመሰረተ እውነተኛ ድጋፍ አልነበረም።

ነገር ግን፣ አሁን እነዚህን ሁሉ የድጋፍ መሰረቶች ያገለለው ጠ/ሚ፣ ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካዊ ቅቡልነት ቀውስ ውስጥ ገብቷል። እያየለ የመጣውን የታጋዮች ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ ማዕበል ለመቋቋምና ለመቅረፍ በሚል ተስፈኝነት፣ እንደ ኦፌኮ እና ኦነግ ያሉ የኦሮሞ ፖለቲካ ድርጅቶችን የፎቶ ፖለትካ መጠቀሚያ ለማድረግ ዝግጅት ላይ ይገኛል።

የአገዛዙን ፍላጎት እንዲፈጽሙ ለማድረግ፣ አቢይ እና ተባባሪዎቻቸው የብልጽግና ፓርቲ የፓርቲዎቹን “የኣሮሚያ የሽግግር መንግስት” ድርድር ጥያቄ እንደተቀበለ አድርጎ ውሽቶቻቸውን ለኦነግ መሪዎች እየመገቡ ናቸው።  አብይ ስለ “ሽግግር” ሲናገር ስልጣን ውሰዱና ተባብረን አጅቡኝ ማለት እንጂ ስለሃቀኛ ሽግግር እንዳልሆነ ግልጽ ነው። በተመሳሳይ ከኦነሠ (OLA) ጋር ለመወያየት የተለየ ድርድር እንዳለ አድርገው የተለመደው ውሸታቸውን ነግረዋቸዋል። ለማንኛውም አስተዋይ ተመልካች የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት የዚህ አይነት የጓሮ በር ማጭበርበር አካል እንደማይሆን ግልጽ ነው።  በገለልተኛ ሦስተኛ አገር የተደረገ ሰፊና ዓለም አቀፋዊ የሽምግልና ድርድር ሊፈታ ያልቻለውን ጉዳይ፣ ፊንፊኔ ሊደረግ በታሰበው የጓሮ ስምምነት አማካኝነት ሊፈታ አይችልም።

 የአብይ እውነተኛ ዓላማ ግልፅ ነው።

 1ኛ.    የኦሮሞ ፓርቲዎችን እንደ መሳሪያ በመጠቀም በመላ ሀገሪቱ ካለው ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ጫና ለመትረፍ ነው። ይህ ገዥው ቡድን ቀደም ሲል በብሔራዊ ውይይት ኮሚሽን በኩል ለመተግበር ያደረጋቸው ሙከራዎች ተዓማኒነታቸውን ካጡ በኋላ የተወጠነ ሌላ የትብብር (የአጅቡኝ) ስልት ነው። 

 2ኛ. በኢትዮጵያ በተለይም በሰሜን በሚገኙ ሌሎች ብሄሮች እና ህዝቦች ላይ በሚያካሄደው ጦርነት የኦሮሞን ህዝብ ማህበራዊ መሰረቱ አድርጎ ህዝባችን ላይ ጠላት ማብዛት። የኦሮሞን ህዝብ ዋና ማህብራዊ መሰረቱ አስመስሎ ለማቀረብ አብይ አህመድ ብዙ ጥሯል። በቅርቡ ከመከላከያ ኣዛዦች ጋር ባደረገው ስብሰባም ኦሮሚያን ፍጹም ሰላማዊ አስመስሎ ለማቅረብ የዋሻቸው ግትልትል ውሸቶች አንዱ ማሳያ ነው።

 3ኛ.  በኦሮሞ ተቃዋሚዎች መካከል መለያየትን ለመዝራት።

የኦሮሞ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በዚህ ድራማ ለመሳተፍ ከተስማሙ፣ ይህንን ሊያደርጉ የሚችሉት ስለአገዛዙ የምናውቀውን ነገር ሁሉ የሚፃረርና፣ ያለ አንዳች የማስገደድ ዐቅም፣ ያለ አንዳች የሶስተኛ ወገን ታዛቢነት እደሚሆን እሙን ነው።  ይህንን አደገኛ አካሄድ ተገንዝበው በህዝባችን ላይ ከስቃይ በቀር ምንም ያላመጣውን ስርአት ለማንሰራራት መሳሪያ እንዳይሆኑ እያልን የሀገር ሽማግሌዎቻችንን፣ አባ ገዳዎችን እና የፓርቲ አመራሮችን በትህትና እንጠይቃለን። አብይ አህመድ በ2018 በተዘዋዋሪ ያገኘውን ድጋፍ ከሚሊዮኖች ጭፍጨፋው በኋላ አሁንም መልሶ እንዲሞክር መተባበር ታሪካዊ ስህተት ነው።

2.   ህዝባችንን ለመከፋፈል “የባህል ተሃድሶ” መጠቀም

አገዛዙ ሰሞኑን በድንገት “የባህል ተሃድሶ” የሚባል ፕሮግራም በኦሮሚያ ጀመሯል።  ይህ ቡድን የኦሮሞን ባህላዊ እሴቶች፣- ለሰው ልጅ ህይወት ክብር፣ ሰላም ማዕከላዊነት እና የብዙሃነት መቻቻልን ስልታዊ በሆነ መንገድ ያራከሰው እንጂ ሌላ አይደለም። አገዛዙ አሁን የጀመረው “የባህል ተሃድሶ” የሚለው ስሪት እጅግ ዕኩይ ዐላማ ያለው ነው፤- አንዱን የኦሮሞ ክፍል ለይቶ “እውነተኛ የባህል ጠባቂ” አድርጎ በማቅረብ ሌሎች የተወሰኑትን ደግሞ የክርስትና ወይም የእስልምና እምነት ተከታይ በመሆናቸው ምክንያት “ከዳተኞች” ብሎ ፈርጆ የኦሮሞን ህዝብ ለመከፋፈል ይፈልጋል።

አላማው ግልፅ ነው፡ አንዳንዶቹ በባህላዊ ማንነታችን ከሌሎች የበለጠ ትክክለኛ መሆናቸውን በመጥቀስ በኦሮሞ መካከል ጥላቻን መፍጠር ነው።  ይህ ሆን ተብሎ የኦሮሞን ህዝብ አንድነት ለመሸርሸር፣ የኩራታችን ምንጭ ባህላችንን ወደ መለያያ መሳሪያነት ለመቀየር የሚደረግ ሙከራ ነው።

የኦሮሞ ህዝብ እንደ ሁልጊዜው በልዩነት ውስጥ የአንድነት ፋና ወጊ፣ የወጎች/ትውፊቶች ባለቤት፣ በልዩ ልዩ እምነቶች እና ልምዶች የተዋበ ህዝብ ነው። ባህላችን አንድ ብቻ ወይም ነጠላ ሳይሆን፣ ህልው የሆነ፣ ዋና ይዘቱን ጠብቆ፣ Safuu (ሰፉ – የሥነ ምግባራዊ ታማኝነት)፣ Nagaa (ነጋ – ሰላም) እና Walooma (ወሎማ – አብሮነት) ዋና እሴቶቹን እንደጠበቀ የሚያጎለብት እስትንፋስ ያለው ህልው ሀብታችን ነው። አገዛዙ በኦሮሞ ባህል ላይ ጠባብና አግላይ የሆነ ትርጉም ለመስጠት መሞከሩ የማይደዳሰሱ  ቅርሶቻችንን ማራከስ ብቻ ሳይሆን ዐብሮነታችንን ለማዳከም የተሰላ እርምጃ ነው።  

የኦሮሞ ህዝብ እነዚህን የማጭበርበሪያ ዘዴዎች በመጋፈጥ አንድነቱን በንቃት መጠበቅ እና ማረጋገጥ አለበት። የጥንካሬያችን መሠረት ጭቆናን በጋራ በመቃወም እና ለህዝባችን ፍትህ ለማምጣት ያለን ቁርጠኝነት ላይ መሆኑ ግልጽ ነው። አገዛዙ የኦሮሞ ፓርቲዎችን በመከፋፈል እንዲሁም፣ ህዝባችንን ባህል በመበረዝ ለመከፋፈል የሚያደርገው ሙከራ በቆራጥነት ልንቃወመው የሚገባ እኩይ ተግባር ነው። ለኦሮሞ ፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፣ በመርሆቻችሁ ላይ ጸንታችሁ እንዲትቆሙ እና የሕዝባችንን እምነት በተደጋጋሚ ከከዳው አገዛዝ ጋር የሚደረገውን ማንኛውንም ዓይነት ትብብር እንዳትቀበሉ እናሳስባለን። ኦነሠ (OLA) የጭቆና መዋቅሮችን የማፍረስ እና የህዝባችንን ነፃነት የማረጋገጥ ተልእኮውን በጽናት ይቀጥላል። ለፍትህ እና ለነጻነት የሚደረገው ትግል፣ ሳይደናቀፍ፣ አይበገሬነቱን ጠብቆ ቀጥሏል።

የኦነግ-ኦነሠ ከፍተኛ ዕዝ

የካቲት 16፣2025

Leave a Reply

Discover more from Qeerroo Bilisummaa Oromoo

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading