በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት መሪዎች መካከል ተደረገ ስለተባለው የውይይት ድምጽ:- (የኦነግ-ኦነሠ ጋዜጣዊ መግለጫ)
የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊትን ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ለማጥፋት ያለመውና በኢትዮጵያ የሚገኙትን የጸጥታ ሃይሎች ሁሉ በማሰባሰብ “ወሳኝና”፣ “የመጨረሻ” የተባለ ወታደራዊ ዘመቻውን ከ30 ቀናት በላይ ቢያካሂድም በለስ ያልቀናውና ይልቁንም እየተሸነፈ የሚገኘው የአብይ አገዛዝ፣ ወደ ሌላ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ለመዞር የወሰነ ይመስላል። ከኤፕሪል 21 ቀን 2022 ጀምሮ አገዛዙ በአዛዦቻችን ጃል መሮ እና ጃል ሳኚ መካከል ተካሄደ ያለውንና በአብዛኛው ተቆራርጦ የተቀጣጠለ የግማሽ ሰአት የድምጽ ውይይት በሁሉም ሚዲያዎቹ ላይ እያሰራጨና ርካሽ የገፅታ ግንባታ ፕሮፓጋንዳ እየሰራ ይገኛል። የብልጽግና አፈቀላጤዎች የኦነሠ አመራር የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚያደርሰውን ግፍ የሚያረጋግጥ ማስረጃ ከራሳችን መሪዎች አፍ እንዳገኘም ያለአንዳች እፍረት ፕሮፖጋንዳ ሲነዙ ተሰምተዋል።
እንዳለመታደል ሆኖ (ለነሱ) ግን ፕሮፓጋንዳው አልሰራም ወይም በተቃራኒው ለሠራዊቱ ጠቅሞታል። አሁን ይህንን የድምጽ ውይይት እንደ “የክፍለ ዘመኑ ቅሌት” ቆጥረው በገፍ እያሰራጩ ያሉት የገዥው መንግሥት ሚዲያዎች እነዚህኑ አዛዦች ከአንድ አመት በፊት “ደጋግመው ሞተዋል” ወይም “ተገድለዋል” በማለት አውጀው እንደነበር የዘነጉት ይመስላል። ለምሳሌ ጃል መሮን ለሰባት ጊዜ ገድለው አስነስተው የኢየሱስ ክርስቶስን መለኮታዊ ሀይል አላብሰውታል:: ይሄ አሀዝ በኛ በኩል ከገዥው ሚዲያ የሚወጡትን የማያልቁ የውሸት ጅረቶች ትኩረት እንድንሰጥ ከተጠነቀቅንበት ጊዜ ጀምሮ ባለው ቆጠራ ላይ ብቻ የተመሠረተ ነው። ዛሬም በሀገሪቱ ክርስቲያኖች ዘንድ እየተከበረ ያለውን የትንሳኤ በዓል አስታከው ሌላ የጃል መሮን ትንሳኤ አክብረዋል:: የዚህም ምክንያቱ በቅርቡ በኦሮሚያ የታወጀውና ለአንድ ወር ያለውጤትና በወራሪው ሽንፈት እንዲሁም ሲቪሎችን በመግደልና በማሰቃየት ብቻ የዘለቀው ወታደራዊ ዘመቻ ፍጹም በመክሸፉ በርካሽ ፕሮፓጋንዳ ለማሽሞንሞን ታስቦ መሆኑ ነው።
ይህን ካልን በኋላ፣ ስለ ተባለው ኦዲዮ ውይይቱ ራሱ ጥቂት ነጥቦችን እንመልከት።
1ኛ. በድምፅ ቅጂው የተወሰነውና ተቆርጦ ከተቀጠለው ውጪ ያለው ውይይት ከረጅም ጊዜ በፊት የተደረገና የአመራሩን ወቅታዊ ሁኔታ በፍፁም የማያንፀባርቅ ነው። ከዚህ አንፃር የድምጽ ምልልሱ አሁን ካለው ሁኔታ ጋር በምንም መልኩ አይገናኝም። በአሁኑ ሰአት የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት በውይይቱ የተንፀባረቁ የተወሰኑ ችግሮቹን ቀድሞ በመፍታት ‘ወሳኝ’ ለተባለው ዘመቻ የተላከውን የአገዛዙን ጦር በሁሉም ግንባሮች – በምእራብ፣ መካከለኛው እና ደቡብ ግንባሮች በመምታት ተጨማሪ ድሎችን በማስመዝገብ ላይ ይገኛል። የስኬቶቻችን አንዱ ምክንያትም በትግሉላይ የነበሩ የተወሰኑ ጎታች ችግሮችን ከዘመቻው በፊት በመፍታት መዘጋጀታችን ነበር::
2ኛ. አገዛዙ ይጠቅመናል ብሎ ቆርጦና ቀጥሎ በለቀቀው ውይይት ላይም ቢሆን ሁለቱ አዛዦች ከንቅናቄያችን መሰረታዊ መርሆች በተቃራኒ እና ከህዝባችን ፍላጎት ውጪ በትግሉ ውስጥ የተከሰቱና የሚከሰቱ ችግሮችን እንዴት በተሻለ መንገድ በመፍታት ወደፊት መሄድ እንዳለባቸው ነበር የተወያዩት:: ከነዚህም መሀከል አንዳንድ የኦነግ ተዋጊዎችን በማስመሰል በመንግሥት ሥምሪትና በሽፍታነት የሚንቀሳቀሱ ሰርጎ ገቦችን እና አላማቸውን በግል ጥቅማቸውና ዋልጌነታቸው ሲሉ ከሳቱ ጥቂት አባላትን የሚያፀዱበትን መንገድ የሚመለከት ነበር:: አዛዦቹም እነዚህን እኩይ አካላት በህዝባችን ላይ የሚደርሱትን ማንኛውንም ጥቃት በእርግጠኝነት እና በግልፅ ቋንቋ ደጋግመው አውግዘዋል። ለተፈፃሚነቱም ቁርጠኝነታቸውን አሳይተዋል::
3ኛ. ንግግሩ በጥሞና እና በዐውደ ርዕይ ከተደመጠ፣ አዛዦቻችን ከአላማው ያፈነገጠ ጦር እና ሠርጎ ገቦች ላይ ያላቸውን ይቅርታ የለሽ አቋምና ለህዝባቸውም ከአንድ ወታደር ሊኖር ይችላል ተብሎ የማይገመት ርህራሄ ያላቸውና ህዝባችንንም ከተመሳሳይ ጉዳት ለመታደግ ምን ያህል ዝግጁ እንደሆኑ በግልፅ የሚያሳይ ነው። በዚህ የተከበረ የነፃነት ትግል ውስጥ የኦነሠ አመራር የሰራዊታችን አባልም ይሁን ተመሳስለው በገዥው አካል የተላኩ ሠርጎ ገቦች ሰላማዊ ዜጎችን ለመጉዳት ወይም እንቅስቃሴያችንን ለማንኳሰስ የሚፈፅሙትን አንዳችም ተግባር እንደማይታገሱ ይጠቁማል።
4ኛ. ከንግግራቸውም በግልፅ የሚታየው እጅግ ሥርአትና ግብረ ገብነት የተሞላበት ውይይት መሆኑ ነበር:: ንግግሩ ከጭቅጭቅ ይልቅ ውይይትንና መደማመጥን የተከተለ ሲሆን ይሄውም የቆየውን የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ የውይይትና (elaa fi elaamee) ምክክርን ባህልን ያረጋገጠ ብቻሳይሆን የወታደራዊ ዕዝን የአዛዥ ታዛዥ ሥርአትንም የተከተለ ነበር:: ገዢው መንግሥትና እሱም የሚመራው ሥርአተ አልበኛ ሠራዊት ከዚህ ውይይት ብዙ መማር ይገባቸዋል እንላለን::
በመጨረሻም ለመላው የኦሮሞ ወዳጆችና ጠላቶችም መግለፅ የምንፈልገው ነገር ቢኖር በአገር ውስጥም ሆነ በዲያስፖራ የሚኖረው ህዛባችን የኦነግ – ኦነሠን መሪዎች ጥንካሬ እና ውስንነት በቅርበትና በአግባቡ እንደሚያውቋቸው ነው:: ይሄ አመራር የማይታለፉ የሚመስሉ አያሌ ተግዳሮቶች ሲገጥሟቸው በምን አይነት ጥበብና ቁርጠኝነት አልፈው ትግሉን አሁን ላለበት የማይናወጥ ደረጃ እንዳደረሱት ህዝባችን ከቅርብና ከሩቅ በተደጋጋሚ አይቷል። በአዛዦቻችን እና በሚመሩትም ሠራዊት እጅጉን ይኮራል። ለዚህም ነው ህዝባችን ሁሉንም አይነት መስዋዕትነት ጭምር በመክፈል ሠራዊቱን የሚደግፈው። ለዚህም ነው ምንም አይነት የአገዛዙ ፕሮፓጋንዳ ይሄን የሠራዊታችንና የኦሮሞን ህዝብ መስተጋብር ሊለውጠውም ይሁን በትግሉ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ መፍጠር ያልቻለው፣ ለወደፊትም አይቻለዉም::
ድል ለኦሮሞ እና ለተጨቆኑ ህዝቦች በሙሉ!
የኦነግ-ኦነሠ ከፍተኛው ዕዝ
ኤፕሪል 22፣ 2022


