• Wed. May 13th, 2026

በኦሮሞ ነጻነት ግንባር – ኦሮሞ ነጻነት ሰራዊትና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል በታንዛኒያ ለ2ኛ ዙር ተደረጎ የነበረዉን የሰላም ድርድር አስመልክቶ በኦነግ-ኦነሰ ዋና አዛዥ ጃል መሮ ዲሪባ የተሰጠ ማብራርያ

Apr 23, 2024

«የድርድሩ ሂደት እንዴት ነበር? የነበረዉስ ተግዳሮት? በእዉነት በእርቅ እንጨርሰዋለን ብላችሁ ነበር የሄዳችሁት? ከዚህ የድርድር ሂደት ላይስ የተገኘ ወጤትና ኪሳራስ በተለይ ህዝቡ ማወቅ ያለበትና ለህዝቡ መገለጽ ያለበት ምንድነዉ? እንደ ድርጅትስ ከድርድሩ ሂደት የተገኘዉ ግንዛቤ ምንድነዉ?» ተብሎ በአራታ ቢዮሌሳ ኦሮሚያ ላይ ለቀረበለት ጥያቄ ጃል መሮ ዲሪባ በአፋን ኦሮሞ የሰጠዉ ምላሽ በፀጋዬ ሃይሉ ባልቻ በሚከተለዉ መልኩ ተተርጉሞኣል።
:::::::::::::::::::::::::::::::::::::::::::::::::::::::::::::::::::::::::::::::::::::::::::::::::::

ጃል መሮ ዲሪባ

«እንደሚታወቀዉ ባለፈዉ ጊዜ ከግንባር ወደ ታንዛንያ ለድርድር የተጓዝን ጓዶች ነበርን። ያለዉን ችግር በእርቅ ለመፍታት አምናችሁ ነበር ወይ የሄዳችሁት? ላልከዉ; ስለእዉነት ከሆነ ያለዉን ችግር በእርቅ እንፈታለን ይሳካል ብለን አምነንም ሆነ ባናምንም የህዝባችንን ችግር ለመፍታት እድሉ ካለ በእዉነትም በምንም በኩል ቢሆን የህዝባችን ችግር መፍትሔ እንዲያገኝ ስለምንፈልግ ያዉ መሄዳችን የግድ ነበር።

ይሄ አምባገነናዊ መንግስት ‘በጠረጴዛ ዙርያ ተወያይቼ ችግርን እፈታለሁ’ ብሎ ፍላጎት እስካሳየ ድረስ እኛ መሳተፋችን ችግር የለዉም። ህዝባችን የጠየቀዉ የመብት ጥያቄ ምላሽ ሳያገኝ በመቅረቱ ስለሆነ ጠመንጃ ለማንሳት የተገደድነዉ አሁን ደግሞ ለዚያ ችግር በድርድር እልባት እንሰጠዋለን ሲባል ያንን እድል ማየት ያው ግዴታ ነበር ማለት ነዉ። ስለዚህ እዉነት ይሰካል ተብሎ ቢታመንበትም ባይታመንበትም እድሉ ካለና የኦሮሞ ህዝብ የጠየቀዉ የመብት ጥያቄ ምላሽ የሚያገኝ ከሆነ መሳተፋችን የሚኖረዉ ኪሳራም አልነበረም።

‘ድርድሩ እንዴት ነበር’ የሚለዉን ከነካካን ህዝቡም ምን ማወቅ ይኖርበታል የሚለዉን አይተን መግለጽ ካስፈለገ; የዚህ የድርድር ሂደት ከተጀመረ ሰንበትበት ብሏል:: በመካከላችን በነበሩ ቡድኖች በኩል ‘መነጋገር አለባችሁ የሀገሪቱ ዉስብስብ ችግር በተለይም ይህን ትልቅ ህዝብ የኦሮሞን ህዝብ የሚያጠቃልለዉ ችግር መፍትሔ ማግኘት አለበት’ የሚለዉ ጥያቄ በተደጋጋሚ ሲቀርብልን ቆይቷል። ለሁለት አመታት በላይ በመካከላችን ሲመላለሱ የነበሩ ወገኖች ነበሩ። እንጊዲህ በዚያ ጊዜ ይኼ የሀገሪቱ አምባገነናዊ መንግስት በሰላማዊ መንገድ ችግርን በዉይይት የመፍታትን በር ለረዥም ጊዜ ዘግቶ ከቆየ በዃላ ከተደጋጋሚ ጥረት በዃላ እስቲ እንሞክራለን ተገናኝተን እንሞክራለን በማለታቸዉ እድሉ የተገኘበት ጊዜ ነበር።

ነገር ግን ይሄ እድል እየተገኘ በነበረበት ሁኔታ ዉስጥ የሰሜኑ ጦርነት በዚህ የኢትዮጵያ አምባገነናዊ መንግስትና በቀድሞዉ አምባገነናዊ መንግስት ህዋሃት መካከል ተቀስቅሶ ሀገሪቱ በከፍተኛ ጦርነት ዉስጥ ተዘፈቀች። እኛም ያዉ የዚያም ጦርነት አካል ነበርን ምክንያቱም ከዚያም በፊትም ጀምሮ እስከዛሬ ድርስ ቀጥሎ ያለ ከስርኣቱ ጋር በጦርነት ላይ ስለምንገኝ ማለቴ ነዉ። ከዛ ጦርነት በዃላ ደግሞ እርቅ በአምባገኑ መንግስትና በህዋሃት መካከል እንዲፈጸም የሚል ከፍተኛ ጥረት ነበር። በዚያም የእርቅ ሂደት ዉስጥ ደግሞ እኛም እንድናከፈል ተጋብዘን ነበር። ሌሎችም ብዙ አካላት ነበሩ:: እንደሚታወቀዉ ሌሎችንም ጨምሮ ከህዋሃትም ጋር ቅንጂት ፈጥረን ስለነበር የዚያም ቅንጂት አካላት እንዲሳተፉ ተብሎ ነበር። ያ ግን ሊሆን አልቻለም። በዚያን ሁኔታ ዉስጥ አብረዉ መታየት የማይችሉ ጉዳዮች ነበሩ። አንደኛ የኦሮሞ ህዝብና የሰሜኑ ሀገሪቱ ክፍል ችግር አይመሳሰልም፣ የምንፈልገዉም በፍጹም አይመሳሰልም፣ ሁለተኛ የችግሩም አነሳስ የእኛና የትግራይ ህዝብ ችግር አነሳስ እንደማይመሳሰል ይታወቃል። ደግሞ በወቅቱ በትግራይ ዉስጥ የተፈጠረዉ ሁኔታ እጅግ ከባድ ሆኖ ከጦርነቱም ተሳታፊዎች አኳያና በተጫማሪም በሀገሪቱ ህዝብ ላይ ረሃብን ያመጣ፣ ድርቅን ጨምሮ ዘግናኝ እልቂትን ያስከተለ ጦርነት ከመሆኑም በላይ ከመንግስቱም በተጨማሪ ሌላም አካል ወደ ሀገሪቱ ገብቶ እንደ ኤርትራ መንግስት፣ እንዲሁም የአማራ ሃይሎችና የፌደራል መንግስት ብለዉ ራሳቸዉን የሚጠሩ አካላትን ጨምሮ በትግራይ ህዝብ ላይ ያካሄዱት ጦርነት እጅግ ከብዶ የትግራይ ህዝብ ከባድ መከበብ ዉስጥ በመግባቱ ለከፍተኛ ችግር ተጋልጦ እንደነበረ ሁሉም የሚያዉቀዉ የቅርብ ጊዜ ትዉስታ ነዉ።

በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ዉስጥ የሚደረግ ድርድርና ከኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት – ኦሮሞ ነጻነት ግንባር ጋር የሚደረግ የኦሮሞ ነጻነት ትግል ድርድር የተለየ ስለነበረ እነዚህን ሁለቱን በአንድ አምጥቶ ለመፍታት የሚሞከርበት ሁኔታ ስላልነበረ የእነሱ እንደ አስቸዃይ ወይንም አጣዳፊ ሆኖ ታይቶ በፍጥነት እልባት ሊሰጠዉ ይገባል የሚል አመለካከት ነበር የነበረዉ። ከዚህም የተነሳና እነሱም ከዚያ ድንገተኛ ሁኔታ ዉስጥ በአስቸኳይ መዉጣት ይፈልጉ ስለነበረ ደግሞም በእንደዛ አይነት ሁኔታ ዉስጥ እነዚህን የተለያዩ ችግሮች በአንድ መፍታት አዳጋች እንደሚሆን ስለታመነ በቅደም ተከተል መፍትሔ ለማግኘት መሞክሩ ጥሩ አማራጭ ሆኖ በመገኘቱ ቅድሚያ ለትግራይ ህዝብ ተሰጠ።

ከዚያም የሰሜኑ ጦርነት በዚያን መልኩ ፍጻሜ እንዳገኘ ቀጣይ ሂደቶች መንቀሳቀስ ጀመሩ። ያዉ የሰሜኑ ጦርነት እርቁንም በተመለከተ ህዝቡ የማያዉቀዉ የምናዉቀዉ ነገር እንዳለ ሆኖ ማለት ነዉ። ለምን ቢባል እስከዛሬም ምን እየሆነ እንዳለ እናዉቃለን; እርቁ ለምንድነዉ የተደረገዉ? የተደረገዉስ እርቅ ነበር ወይ? እና በፕሪቶሪያ የተደረሰዉና የተፈረመዉ ስምምነትስ ለህዝብ የተገለጸዉና ከጀርባስ የተስማሙበት ደግሞ ምን ነበር? የሚለዉና በተግባር ላይ የዋለዉስ ምን ነበር? የሚለዉን ጨምሮ ሌሎችም ብዙ ጉዳዮች አሉ። ያንን እንዳለ ትተን ወደ ራሳችን ጉዳይ ስንመለስ; የኛንም ጉዳይ ድርድሩን ቀጥሉ ፍጻሜ ስጡት ሲባል ያዉ ያ አዕምሮዉ ጤነኛ ያልሆነዉ ሰው አብይ አህመድ ያለዉ ነገር ነበር። በሌሎች አከባቢዎች ያለዉ ጦርነት ሳይሆን የጸጥታ ችግር ነዉ ነበር ያለዉ። እነሱ እንደሚሉት ቢያንስ ቢያንስ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብን ነብስ ያጠፋን ጦርነት የጸጥታ ችግር ብለዉ ጠርተዉ ‘መንግስት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል አጋጥሞ የነበረዉን የጸጥታ ችግር ተከትሎ ህግ ለማስከበር ተንቀሳቅሶ በነበረበት ጊዜ ትንሽ ስርኣት-አልበኝነት በተለያዩ አከባቢዎች አጋጠመ እንጂ ሌላ ጦርነት የለም:: ይህንን ስርኣት-አልበኝነት ደግሞ በአጭር ጊዜ ዉስጥ መፍትሔ ልንሰጠዉ እንችላለን በማለት አብይ አህመድ ያንን ያለዉን ችግር በሂደት መፍታት የሚለዉን ለአለም አቀፍ አካላት አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች የገባዉን ቃልኪዳን ጥሶ በአጭር ጊዜ ዉስጥ አሁን በተለያዩ አካባቢዎች ያጋጠሙትን ስርኣት አልበኝነት ፍጻሜ እሰጠዋለሁ በሚል ህልም እንሄድበታለን የተባለዉን ድርድር አሻፈረኝ በማለት ሙሉ በሙሉ ፊቱን ወደ ጦርነት አዞረ።

ወቅቱ ለአብዛኛዉ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊትና የኦሮሞ ህዝብ የነጻነት ትግል ወዳጆች የጭንቅ ጊዜ ነበር:: በአንፃሩ ደግሞ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊትን መጥፋት ለሚመኙ ሰዎችና ቡድኖች ደግሞ የደስታ ጊዜ ነበር። እንጊዲህ ወዳጆች ‘መንግስት በብዙ የቤት ስራዎች ዉስጥ ተጠምዶ ነበር አሁን ከዚያ አገግሞኣልና የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት አሁን የሚከፈትበትን ጦርነት መቋቋም አይችል ይሆናል’ ብለዉ ስጋት ሲገባቸዉ፤ ጠላት የሆኑት ደግሞ ‘የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት መጥፍያ አሁን ነዉ’ ብለዉ የቋመጡበት ጊዜ ነበር። እንጊዲህ እንደዚህ አይነት ተቃራኒ የሆኑ ሁለት ሃሳቦች በሰፊዉ ሲሄዱ ነበር። ጭንቀትም ይሁን ደስታ ሁለቱም የሆነ ነገር ግን አልነበረም። እንደታየዉ እስከአሁንም ጦርነቱም እንደቀጠለ ነዉ። ሁሉን ነገር በጉልበት ማስፈጸም የሚፈልገዉ ይኼ አምባገነናዊ መንግስት ትልቅ ሃይሉን ወደ እኛ መልሶ ትልቅ ዘመቻ፣ ትልቅ ጦርነት ቢከፍትም የቀየረዉ ነገር ግን አልነበረም። የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ከቀድሞዉ ይበልጥ ገዝፎ በጦር መሳርያም ሆነ በሰዉ ሃይል እንዲሁም በችግር አፈታቱ የበለጠ እየተጠናከረ መጣ።

እንጊዲህ በመካከላችን በመመላለስ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩትም ወገኖች ‘ይህ ችግር በዚህ መልኩ ፍጻሜ አያገኝምና በሰላማዊ መንገድ መፍትሔ መፈለግ አለባችሁ ጦርነት መቀጠል የለበትም; መንግስት በሆደ-ሰፊነት ሄዶ የሰሜኑን ችግር መፍትሔ እንደሰጠ አሁንም ሆደ-ሰፊ መሆን ይኖርበታል’ ምናምን ብለዉ እያባበሉኣቸዉ ነበር። ያዉ ዲፕሎማቶች ስለሆኑ የዲፕሎማሲ ቋንቋን ነዉ የሚጠቀሙት::

እኛ ግን ያ ተከፍቶብን የነበረዉም ሰፊ ዘመቻ ያደረገን ነገር የለም፣ በመላዉ ኦሮሚያ ህዝባችን ያቀረበዉ የመብት ጥያቄ ምላሽ በማጣቱ ጠመንጃ አንስቶ የጀመረዉን የነጻነት ትግል በግዝፈትና በጥንካሬ ቀጠሎበት ያንን አምባገነናዊ መንግስት በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲቀመጥ ወደ ማስገደድ ደረጃ ደረሰ። መንግስትም ‘ጊዜ ወስጄ በመላዉ ሀገሪቱ ዉስጥ በተለያዩ አከባቢዎች ያጋጠመዉን የጸጥታ ችግሮች እፈታለሁ በቅደም ተከተል መፍትሔ እንዲያገኙ እሰራለሁ መረጋጋትን አመጣለሁ’ ብሎ ቃል ገብቶ የነበረዉን ቃልኪዳን መጠበቅ አቃተዉ:: ሀገሪቱም በየቀኑ ወደ አዘቅት እየሄደች ስለነበር ከዚህ ዉስጥ ለመዉጣት የግድ ወደ ድርድር ለመምጣት ተገደደ። በዚህ ሁኔታ ነበር እንጊዲህ ‘ተገናኙ ተነጋገሩ’ ተብሎ የመጀመርያዉ ዙር ድርድር የተደረገዉ። በዚያም ድርድር ወቅት የነበረዉ ሁኔታ ብዙ ከባድ ችግሮች ነበሩ። የኦሮሞ ህዝብ የሚያቀርበዉ ጥያቄ በጠረጴዛ ዙርያ ቀርቦ ዉይይት ሳይደረግበት ‘የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ቀድሞ ትጥቅ መፍታት አለበት’ የሚል አጀንዳ ነበር መንግስት ይዞ የቀረበዉ። ህልማቸዉም ያ ብቻ ነበር። ከዚያ ዉጪ በእጃቸዉ ይዘዉት የቀረቡት ምንም አይነት ረቂቅ አልነበረም። ስለዚህ የሚያግባባ ነገር ለማግኘት ከባድ ነበር። ችግርን መፍታት ይቅርና ፊትለፊት የመገናኘቱም መንፈስ እጅግ ከባድ ነበር። በዚህ ሁኔታ ዉስጥ የኛም ቡድን ሄዶ መነጋገር የተቻለዉን ያክል ተነጋግሮ እንጊዲህ ቢያንስ ቢያንስ እንደዚህ መገናኘት ችለናልና ይኼንን እድል ከንቱ አናደርገዉም መግባባት እንኳን ባይቻልም መገናኘቱም ራሱ አንድ መግባባት ነዉና የኦሮሞ ህዝብም ብዙ ይጠብቅብናል ተብሎ በመልካም መንፈስ ተመልሶ ለመገኘት በመስማማት ተጠናቀቀ። በዚያ መልሶ የመገናኘት ሂደት ዉስጥም እንጊዲህ ብዙ የዉንጀላ ፕሮፓጋንዳ ነበር። ነገር ግን የኦሮሞ ነጻነት ግንባር – የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ያንን ሁሉ ተቋቁሞ ለሁለተኛዉ ዙር ድርድር ደረሰ ማለት ነዉ።

የሁለተኛ ዙሩ ድርድር ሲደርስ እኛ በታንዛኒያ ሳንገናኝ አስቀድሞ አንድ ወደ ጄኔቭ ያመራ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር – የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ልኡካን ቡድን ነበር። በጄኔቫም መንግስት በበኩሉ ‘ትጥቅ ፍቱ’ እያላችሁ ነዉ እናንተ ደግሞ በበኩላችሁ ‘ትጥቅ አንፈታም’ ብላችዃል እንጊዲህ እንዴት አድርገን በምን ሁኔታ ልናቀራርባችሁ እንችላለን? ብለዉ ጠየቁን። እነዚህ በመካከላችን የነበሩ አካላት በጄኔቫ ረዥም ጊዜ ወስደዉ ‘የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ምን ሃሳብ አለዉ? ምን ትላላችሁ?’ በማለት ድርድሩ የሚካሄድበትን ሮድማፕ ለማዘጋጀት ሰፊ ዉይይት ሲደረግ ቆየ። በዚህም በጄኔቫ የነበረዉ ልኡካን ቡድናችን በእኛና በመንግስት መካከል ከነበሩት አሸማጋዮች ጋርና በአፍሪካ ቀንድ የየራሳቸዉ የተለያዩ ፍላጎቶች ካሉኣቸዉ መንግስታት ጋር በተደረገዉ ንግግር መተማመን ላይ በመደረሱ ነዉ እንጊዲህ ለሁለተኛዉ ዙር ድርድር ወደ ታንዛኒያ የተኬደዉ። ስለዚህ እኛ ሳንሄድ ቀደም ብሎ ከጥቅምት 16/2024 ጀምሮ እኛ እስከሄድንበት ህዳር 7/2024 ድረስ ማለትም ወደ ወር ለሚጠጋ ጊዜ ያክል ንግግር ሲደረግ ነበር። በዚያ ንግግር ላይ በቅድሚያ በግትርነት የቀረበዉ መንግስት DDR ማለትም Disarm, Demobilize and Reintegrate ብሎ የነበረዉን አቋሙን ትተናል በማለታቸዉ ማለትም ‘ትጥቅ ማስፈታት’፣
‘ህዝብ ዉስጥ መበተን’ና ‘መልሶ ማቋቋም’ የሚለዉ አቋማችንን እሺ አንስተናል በማለታቸዉ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር – የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ልኮት ከነበረዉ ልኡካን ቡድን ጋር ስምምነት ላይ ተደረሰ ማለት ነዉ። በዚህ ላይ መግባባት ላይ ከተደረሰ በዃላ እንጊዲህ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ትጥቅ ሳይፈታ ደግሞ በምን መልኩ ሀገሪቱ ዉስጥ የመንግስት አካል ሆኖ የኦሮሞን ህዝብ ጥያቄ መመለስ ይችላል ሲባል ይኼንን እንጊዲህ ወታደራዊ መሪዎች ናቸዉ የሚያዉቁት ተብሎ ወታደራዊ አመራሮች ተገናኝተዉ ይህንን ጉዳይ ማለትም ትጥቅ ሳይፈታ በምን መልኩ ችግሩ መፍትሔ ሊያገኝ ይችላል የሚለዉ ጉዳይ ላይ ተነጋግረዉ መፍትሔ ያብጁለት ተባለ።

እንጊዲህ እኛ ወክለን የላክነዉ ቀድሞ የደረሰዉ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት – የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ልኡካን ቡድን በዚያ መድረክ እዚህ ደረጃ ያደረሰዉን ድል ፍጻሜ ላይ ለማድረስና በመጨረሻም ሌሎች የቀሩ የተባሉ ችግሮችን ለመፍታት እኛ እዚያ እንድንገኝ ሃሳብ ቀረበ ማለት ነዉ። እዉነቱን ለመናገር የኦሮሞ ነጻነት ትግል ለብዙ ዙሮች ተደናቅፎ ሲወድቅ ሲነሳ ነበር፣ ብዙ መከዳቶች ነበሩ፣ ይህ ደግሞ ያሳስብ ነበር። ከጃል ገመቹ አቦዬ ከጓዴ ጋር ሲንነጋገር ቆይተናል፣ ‘ይህ ጉዳይ እንዴት ይሁን ጃል ገሜ’ ስለዉ

‘እንግዲህ ከቤት የወጣነዉ ለመሰዋት እስከሆነ ድረስ ይህ የጦር ሜዳ ነዉ; በጦር ሜዳ ዉስጥ ደግሞ ታጋይ ጠመንጃ ተተኩሶበት በጠመንጃ ብቻ አይደለም የሚሰዋዉ ሺኒጋም የነበረዉ ያዉ እንደዛዉ ነበር የኦሮሞን ህዝብ ችግር መፍታት በጠመንጃ ብቻ አይደለም በተገኘዉ መንገድ ሁሉ የህዝባችንን ችግር ለመፍታት የሚቻል ከሆነ ለመፍታት ካልቻልን ደግሞ ልንሰዋለት ነዉና ከቤታችን የወጣነዉ እንሄዳለን’
አለ። ሁለታችንም ተስማማን። በዚህ መልኩ ዉሳኔ ላይ ደርሰን ሁለታችንም እንሄዳለን አልን ማለት ነዉ::

በመካከላችን ያለዉ አደራዳሪ አካል ሂሊኮፕተርና fix during የICRC (International Committee of the Red Cross) አይሮፕላን ተከራይቶ ጉዞዉም በምን መልኩ መሆን እንድሚችል መግለጫ ተሰጠን:: ስምምነትም ተፈረመና በምን መልኩ ከሀገር እንድምን ወጣና በዃላም ወደ ሀገር እንደምንመለስ የሚያሳይ የሚያሳምነን ነገር ተገኝቶ ወደ ታንዛኒያ ተንቀሳቀስን ማለት ነዉ።

በታንዛንያም ቀድሞ በስፍራዉ ከነበረዉ ልኡካን ቡድናችን ጋር ከጓዶቻችን ጋር ተገናኘን። ከዚያ ከዚህ አምባገነናዊ መንግስት ጋር በጠረጴዛ ዙርያ ለመቀመጥ በስፍራዉ ተገኘን። ከዚህ አምባገነናዊ መንግስት ጋር ለመወያየት ስንቀርብ የገጠመን ያልተጠበቀ ጉዳይ ነበር። ያልታሰበ ነገር ነዉ የገጠመን። እኛ ሄደን ቀርበን የገኘናቸዉ ሰዎች ሁኔታም የልተጠበቀ ነበር። ግራ የሚያጋባ ነበር። ከዚህ በፊት መግባባት ተደርሶበት የነበረዉን ነገር ነዉ ‘ትጥቅ መፍታት የሚባል ነገር የለም ትጥቅ ሳይፈታ በምን መልኩ ወደፊት መሄድ እንደሚቻል ደግሞ ያላችሁን ሮድ ማፕ አቅርቡ’ ተብሎ የነበረዉን ወደ ዃላ መልሰዉ ቀረቡ።

እኛ ለነገሩ የምንሄድበት ነገር የማይሆን ከሆነስ በምን መልኩ ነዉ የምንመለሰዉ የሚለዉንም ጉዳይ አስተካክለን ስለነበረ ነዉ እንጂ የነሱ ሃሳብ የነበረዉ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊትንና መሪዎቹን መነጣጠል ነበር እንጂ በትክክል ለነበረዉ ችግር በድርድር መፍትሔ ለመፈለግም አልነበረም። ለእርቅ አልነበረም። በመካከላችን የነበሩት አደራዳሪዎች እንኳን ተቸገሩ:: መወያያችን ሊሆን የሚገባዉ RRI ነበር የነበረዉ። DDR ማለትም ያ ትጥቅ ማስፈታት፣ ወደ ህዝቡ መመለስ የሚለዉ ነገር ታልፎ እኛ ያቀረብለዉ RRI ማለትም reorient ማድረግ retrain ማድረግ ከዚያም integret to security sector ወይንም በጸጥታ መዋቅሩ ዉስጥ integret ማድረግ ነበር የነበረዉ ስምምነት። ይህንን ማድረግ ማለት ደግሞ እንደገና ታሰለጥናለህ፣ እንደገና ተሃድሶ ትሰጣለህ፣ ከዚያ በዃላ በሀገሪቱ ተቋማት ዉስጥ የተለያዩ የጸጥታ መዋቅሮች አሉ በነዚያ የተለያዩ መዋቅሮች ዉስጥ ታስገባለህ ማለት ነዉ። እኛ ደግመን የምናሰለጥንበት ምክንያት ደግሞ ሰራዊቱ የተለያየ አመለካከት ላይ ነዉ የሰለጠነዉ፣ አምባገነናዊው መንግስት ያሰለጠነበት የራሱ አጀንዳዎች አሉት፣ እኛም ሰራዊታችንን ያሰለጠንበት አላማ አለን።
እንጊዲህ ይህንን ነዉ reorient አድርገን retrain አድርገን integret እናደርጋለን የሚል ሮድማፕ ላይ ነበር
የተስማማነዉ። በድጋሚ ተሃድሶ የሚወስደዉና በድጋሚ ስልጠና የሚወስደዉ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብቻ አይደለም። በዚህ ላይ መግባባት አልተቻለም። የሚያሰለጥነዉስ ማን ነዉ? ወደ ማሰልጠኛ ካምፕ ሲገባስ በምን መልኩ ነዉ? ሲገባስ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት የታጠቀዉ መሳርያም ሆነ የመንግስት ወታደር የታጠቀዉ የጦር መሳርያስ ምን መሆን አለበት? ማን ነዉ መያዝ ያለበት? ቁልፉን ማን ነዉ መያዝ ያለበት? በማን እጅ ነዉ መቀመጥ ያለበት? ስልጠናዉስ ሲሰጥ የምንሰጠዉ ስልጠናስ ምንድነዉ? መንግስት የሚፈልገዉ ሁልጊዜ አንድ ላይ ሰብስቦ ወደ ካምፕ አስገብቶ የፈለገዉን አስተምሮ መልቀቅ ነዉ። እኛ ደግሞ ይኼ አይሆንም አልን። መሆን ያለበት ይኼም መንግስት ሆነ እኛም ሰራዊታችንን የሀገር ሰራዊት ማድረግ ነዉ የሚያስፈልገዉ አልን። ሰራዊቱ የፓርቲ ወይንም የመንግስት ሰራዊት እንዳይሆን አድርገን የሀገር ሰራዊት መሆን አለበት ነዉ ያልነዉ።

አሁን ካየህ በዚህ ሀገር ዉስጥ ያለዉ ሰራዊት የአምባገነናዊዉ መንግስት ሰራዊትና ገዢዉን ፓርቲ ብቻ ሰራዊት የሚያገለግል ነዉ:: የዚያም ፓርቲ መሪዎች ‘እኛ የማንኖር ከሆነ እናንተም አትኖሩም ስለዚህ በርቱና ተወጉ’ ነዉ የሚሉኣቸዉ። ነገር ግን እንደዛ አይደለም የሀገር ሰራዊት መሆን ያለበት። ዬትኛዉም ፓርቲ የመንግስትን ወንበር በምርጫ ቢያሸንፍ ሰራዊቱ የሀገር ነዉ መሆን የሚገባዉ; ያዉ ልክ እንደሌሎች ዲሞክራሲያዊ ሀገራት ማለት ነዉ። ዬትኛዉም ፓርቲ ከስልጣን ቢወገድ ዬትኛዉም ፓርቲ ወደስልጣን ቢመጣ ሰራዊቱ ይቀጥላል ይኖራል። የሀገር ስለሆነ አይፈርስም። እነሱ ግን ሰራዊታቸዉን በዚህ ነዉ የሚያስፈራሩት። እንደዛ ግን መሆን የለበትም። ስለዚህ ሰራዊትን የሀገር ሰራዊት ማድረግ አለብን ስለዚህ የመንግስትም የኛም reorient የሚደረገትን ሁኔታ በማመቻችት retrain እና integret መደረግ አለበት የሚል ነበር እኛ የያዝነዉ። ለዚህ ደግሞ linkage/ትስስር፣ phase/ደረጃ እና sequence/ቅደም ተከተል አስቀምጠናል።

የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ወደ ስልጠና ሲገባ በሺዎች ትጥቅ ፈቶ በአንድ ጊዜ ስልጠና አይገባም። ይህንን ያደረግንበት ምክንያት በከሃዲዎች ብዙ ጊዜ ስለተከዳን ነዉ፣ ቁስል ስላለብን ነዉ ወደን አይደለም። የግድም እንደዛዉ ነዉ መሆን ያለበት። ግማሹ ያክል ከመንግስት ሰራዊት ጋር ተቀላቅሎ ስልጠና በመግባት መሰልጠን ነዉ ሂደቱ። ስልጠናዉም መንግስት ሲያስልጥን እንደነበረዉ መሆን የለበትም። ለምሳሌ መንግስት ሲያሰለጥን የመንግስት ወታደር ሰዎችን ገድሎ አስክሬን ላይ እስከማስቀመጥ፣ ሰዉን እስከማረድና እንደዛ የመሳሰሉ ነገሮችን ነዉ:: እኛ ግን ማሰልጠን የምንፈልገዉ ዲሞክራሲ፣ እኩልነት፣ የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ፣ ፕሮፌሺናል የሆነ ሰራዊት፣ የፈለገዉ አይነት የፖለቲካ ፓርቲ ምርጫ አሸንፎ ፓርላማ ይግባ፣ በፖለቲካዉ የስልጣን ወንበር ላይ ከፈለገ ጫማ አዉልቆ እርስ በእርስ ይወራወር ሰራዊቱ ግን ሰላምን ማስከበር ነዉ ስራዉ መሆን ያለበት። ከዚያ ዉጪ የሀገር ሰራዊት ለዬትኛዉም መወገን የለበትም። ለዬትኛዉም የፖለቲካ ፓርቲ አይወግንም። ለመንግስት ወይንም ለገዢ ፓርቲ አይወግንም፣ ለተቃዋሚ ፓርቲ አይወግንም። ሰራዊቱ ሀገርን ነዉ የሚጠብቀዉ፣ መንግስት የሆነዉ ፓርቲና ተቃዋሚዉ ሲፎካከሩ ህዝቡ ነዉ የሚያየዉ የሚበጀዉንም ፓርቲ የሚመርጠዉ ህዝቡ ነዉ። ህዝቡ በመረጠዉ መሰረት ደግሞ በስራ ላይ ይዉላል። በስራ ላይ ራሱ እንዲዉል የሚያደርገዉ ሰራዊቱ ሳይሆን የዲሞክራሲና የህግ ተቋማት ይኖራሉ። እነዛ ተቋማት ናቸዉ የሚሰሩት። ይህንን ነዉ እኛ ይዘን የቀረብነዉ። ይህ ግን ለዚያ አምባገነናዊ መንግስት ሊዋጥለት አልቻለም። ይኼ ሀገር ማፍረስ ነዉ አሉ። እዉነታዉ ግን ይኼ ሀገር ማፍረስ አይደለም እንዲያዉም ሀገር መገንባት ነዉ።

ከዚህም አልፈዉ ያሉት ነገር ቢኖር ‘ዲሞክራሲ በአንድ ሌሊት አይመጣም’ ነዉ ያሉት። ‘ዲሞክራሲ በአንድ ሌሊት አይመጣም በዚህ በኳላ-ቀር ህዝብ ዉስጥ’ ነዉ ያሉት። በዚህ ሀገር ዉስጥ ያለዉ ህዝብ ግን ዃላ-ቀር አይደለም ዃላ ቀርስ ሀገሪቱን እያስተዳደረ ያለዉ ቡድን ነዉ። መስከረም 15 ቀን 2018 የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አመራር ከአስመራ ፍንፍኔ የገባ እለት በሚሊዮኖች የሚቆጠር ህዝብ ወጥቶ ፖሊስ በጠመንጃ አይደለም በዱላም ወጥቶ መንገድ ላይ ሲቆም አልነበረም። ለሀገር ሰላም ሰጥተህ መብቱን ካከበርክለት ህዝብ የሚፈልገዉ ነገር የለም:: ለዚያ ደግሞ ከዚያ ክስተት በላይ ማስረጃ ሊሆን የሚችል ነገር የለም። ይህ ነዉ የሆነዉ። ስለዚህ ‘ዲሞክራሲ በአንድ ሌሊት አይመጣም ይህንን ዃላ-ቀር ህዝብ በጉልበት ካልያዝከዉ አይሆንም’ የሚባለዉ ነገር ሲበዛ ቀልድ ነዉ። በሰዉ ቁስል መቀለድ ነዉ ይኼ። ከዚህ የተነሳ መግባባት ላይ መድረስ አልተቻለም።

እኛ ያልነዉ የተወሰነ ሰራዊት ካምፕ ገብቶ ስልጠና ሲጀምር ወይም ኦሬንቴሽን ሲጀምር መንግስት ደግሞ በመቀጠል political commitement/የፖለቲካ ቁርጠኝነት ማሳየት ይኖርበታል ነዉ። አንተ የተወሰነ ሰራዊት ማሰልጠን ስትጀምር መንግስት ደግሞ የተወሰ ቢሮዎችን ለአንተ መክፈት መጀመር ይጠበቅበታል፣ ወደ ህዝባችን ቀርበን ማናገር መቻል፣ ሰራዊት በአንድ ስፍራ ሲሰለጥን መንግስት የሚያሳየዉ political commitement በአንድ ስፍራ እየታየ በዚያ መልኩ phase and sequence ኖሮት በlinkage በማስተሳሰር ወደ ፊት መሄድ ይቻላል ስንል ነዉ እነሱ አሻፋረን ያሉት። ይህንን መቀበል እምቢኝ በማለታቸዉ ሂደት ዉስጥ በመካከላችን የነበሩት አደራዳሪዎች ናቸዉ የተቸገሩት እንጂ የመንግስት ተወካዮች ተሯሩጠዉ ወደ ሆቴል ክፍላቸዉ በመግባት በር ዘግተዉ ነበር የተቀመጡት። እንዴት እንድምናናግራቸዉ እንኳን ነበር ያጣነዉ። ሃሳባችንን እንዴት እንደምናቀብ ነበር ያጣነዉ። እኛ የምናነሳዉን ጉዳይ ሁሉ ‘ይኼንንማ ህገ-መንግስቱ አይፈቅድም’ እያሉ ሮጠዉ በመሸሽ ወደ ሆቴሎቻዉ ይከተታሉ። ያንን ህገ-መንግስት ደግሞ አያዉቁትም::

ብርሃኑ ጁላ አንድ ጊዜ አስቂኝ የሆነ ቃለ-ምልልስ ሲሰጥ ነበር; እጅግ በጣም አስቂኝ። ‘እኔ እኮ እዚያም እዚህም ና እያሉኝ» እያለ ተፈላጊ ነኝ አይነት ቀልድ ሲቀልድ ነበር። ‘በአለም ላይ በጣም ተወዳጅ ተፈላጊ ሆነናል’ ሲል በጣም ነበር ያሳቀን። የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊትን ደግሞ ዬትኛዉንም አለም-አቀፋዊ ህግ አያዉቅም አለ። የአለም አቀፍህጎች ይቅርና በሀገራቸዉ ህገ-መንግስት ላይ ያለዉን እንኳን ጠቅሰን ይኼ ይኼ በምንልበት ጊዜ ‘ይኼንንማ ህገመንግስቱ አይፈቅድም’ ይላሉ። ይኸዉ ህገ-መንግስታችሁ እንደዚህ እንደዚህ ይላል በምንልበት ጊዜ ደግሞ ቁጭ ብለዉ አይወያዩም ይሸሻሉ:: ወደ ሆቴል ክፍሎቻቸዉ ገብተዉ በር ዘግተዉ ይቀመጣሉ። በመካከላችን የነበሩት አደራዳሪዎች በጣም ነበር ግራ የተጋቡት። የራስ-ምታት ነበር የሆነባቸዉ። በዚህ መልኩ እየቀጠለ ባለበት ሁኔታ ዉስጥ ደግሞ የሆነ ጉዳይ አነሱ። ያነሱትም ጉዳይ ‘እስቲ እነዚህን ፈረንጆች ከመካከላችን አዉጡና አብይ የላከላችሁ መልዕክት አለና መልዕክቱን ተቀበሉን’ አሉን። አይ እንደዛ አይነቱን የሁለት አመት እድሜ ህጻናትን በከረሜላ መደለል አይነት ጫወታችሁን እኛ አንጫወትም አልናቸዉ። በብዛት እዛ የነበሩት ሰዎች ስለኦሮሞ የነጻነት ትግል ራሱ የሚያዉቁት ምንም ነገር አልነበራቸዉም። የሬድዋን አይነቱ ሰዉ የሚሰጠዉ ምሳሌ ‘እኔ ለምሳሌ በትግሬዎች ዘመን ስልጤን ወክዬ ከትግሬዎች ጋር ሰርቼ እንደዛ እንደዚህ አደረኩ እናንተም ልክ እንደነ ብርሃኑ፣ እንደነ ቀጄላ፣ ብትሆኑ’ ብሎ የሚያባብል አይነት ሰዉ ነዉ። እንጊዲህ እዛ የነበሩት የነሱ ተደራዳሪዎች እንደነዚህ አይነት ሰዎች ነበሩ። የሀገሪቱን ችግሮች ዉስብስብነት እንኳን የማያዉቁ፣ አብሮ ለመነጋገር እንኳን አስቸጋሪ የሆኑ ማለት ነዉ:: እስቲ እንጊዲህ እሺ ኦፊሴላዊ በልሆነ መልኩ አምስት ደቂቃ እንስጣችሁና ምንድነዉ መልዕክቱ? አልናቸዉ። ጃል ገሜና እኔ ነበርን አብይ መልዕክት ልኮላችዃል ብላችዃል እስቲ መልዕክቱ ምንድነዉ ስንላቸዉ ‘ፈረንጆቹ ፊትለፊት መናገር አንፈልግም’ አሉ። እሺ ችግር የለዉም ነገር ግን ኦፊሴላዊ አይደለም ብለን ሄደን አብረን ለብቻ ተቀመጥን። ከዚያ መልዕክቱ ምንድነዉ ስንላቸዉ ‘ሰራዊታችሁ ትጥቅ አይፈታም አምጡና ወደ መከላከያ ሰራዊቱ ቀላቅሉና አብረን ሆነን ፋኖንና ሸዐቢያን እንወጋለን ለእናንተ ደግሞ ስልጣን እንሰጣችዃለን ብሏል’ አብይ አሉ። በጣም ያስቃል። ይህንን በሚያክል ህዝብ ላይ ቀልድ ነዉ እየቀለዱ ያሉት፣ ተጋሩን ለመዉጋት ከሻዕቢያና ከፋኖ ጋር ተሰለፈ አሁን ደግሞ በግል ጉዳያቸዉ በገቡበት ግጭት ኦሮሞ ደግሞ ከእሱ ጋር ተሰልፎ እነዛን በመዋጋት ደሙን እንዲያፈስለት ይፈልጋል። ለዚያዉም ለመዋጋትም አይደለም እኛን ወጥመድ ዉስጥ የሚያስገባበትን ዘዴ መዘየዱ ነዉ።

እኛ የሀገሪቱን ችግር ለመፍታት ያቀረብነዉን ፋኖንም ጨምሮ የሀገሪቱን ችግር መፍትሔ ለመስጠት ነዉ። እነሱ ደግሞ እኛን ያዩበት ሁኔታ የአማራ ጠላት እንደሆንን አድርገዉ ስለሆነ ይህንን ጉዳይ በቶሎ ተቀብለን ወደ ወጥመዳቸዉ የምንገባላቸዉ አይነት አድርገዉ ነበር። እኛ የሀገሪቱን ችግር ለመፍታት ያቀረብነዉ ሮድማፕ ዉስጥ መንግስት በሀገሪቱ ዉስጥ የሚገኙትን ተቋማት ሌላዉን በፖሊስ፣ በወታደር፣ በደህንነት ሃይል ተቆጣጥሮ እንደፈለገዉ የለምንም ልጓም እየጋለበ ስለሆነ ያ ልጓም ሊበጅለት ይገባል ነዉ። ‘በአንድ ሌሊት አይመጣም ያላችሁትን ዲሞክራሱ’ ደግሞ በአንድ ሌሊት ልምምዱን መጀመር ይቻላል ዛሬ መጀመር እንችላለን ነዉ ያልነዉ። ስለዚህ በሀገሪቱ ዉስጥ ያሉትን ተቋማት ዲሞክራሲያዊ ለማድረግና ነጻ በማድረጉ ላይ መስራት ለሀገሪቱ መሰረታዊ ሰላምን ያመጣል። ያንን ካደረግን በዃላ ደግሞ ተሰባስበን ህዝቡ የፈለገዉን መምረጥ ይችላል። ከዚህም በዃላ አይቆምም የኦሮሞ ነጻነት ትግል። የኦሮሞ ህዝብ ነጻ ወጥቶ በሀገሪቱ ዉስጥ ያሉት ተቋማት ከመድሎ ነጻ ከሆኑ በዃላ የሚቀጥለዉ የኦሮሞ ህዝብ የራሱን እድል በራሱ የመወሰን መብት ማለትም ከፈለገ ከኢትዮጵያ ጋር አብሮ መኖር ወይንም መለያየትን ይወስናል። የኦሮሞ የነጻነት ትግል እስከዚህ ድረስ የሚሄድ ስለሆነ በእንደዚህ ኣይነት ማታለል የሚቆም አይደለም የሚል ነበር መልስ ይሰጠናቸዉ። ይህንን ሲሰሙ መልሰዉ ሸሹን። ሸሽተዉን አንድ ሶስት ቀን ሆቴል ገብተዉ ሲተኙ ከከረሙ በዃላ ደግሞ በመካከላችን የነበሩትን አደራዳሪዎችን ይልካሉ እነሱም ይመጣሉ ይሄዳሉ:: እንደዚሁ እየተባለ ከሶስት ቀናት በዃላ እንጊዲህ የሚደረግ ነገር የለም ሲባል እዚያ የነበሩት አምባሳደሮች በጣም ተቸግረዉ መንግስትን ማስገደድ ጀመሩ።

በግድ ‘ኑ ቁጭ በሉና ተነጋገሩ እነሱ ያቀረቡትን አንቀበልም የምትሉበትንም ምክንያት ተናገሩ’ አሉአቸዉ። በዚህ ጊዜ የተናገሩት በጣም የሚያስቅ ነገር ነበር።

‘የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ስልጣን ነዉ የሚፈልገዉ፣ አንድ ስንዝር መሬት እንኳን ሳይቆጣጠር ስልጣን ይፈልጋል’

በማለት ሌላ በፕሮፓጋንዳ ይዘዉ መጡ። ያንን ቀን እንደ አጋጣሚ ሆኖ አሁን ኢትዮጵያ ያለዉ የአሜሪካ አምባሳደር ማስኒጋ በመካከላችን ነበር። አምባሳደር ማስኒጋም

‘ይኼ መሬት መቆጣጠርን እንኳን እስቲ ተዉት ለምሳሌ እኔ ከፍንፍኔ ወጥቼ ወደላይ ወደነ እንጦጦ መኪናዬን ነድቼ ንጹህ አየር ለመቀበል ፍላጎት አለኝ ነገር ግን አይቻልም’

አለ። ይህ ማለት ይኼ አምባሳደር የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት እሱ ባለበት ስፍራ ያለበትን ደረጃ በዚህ ደረጃ ያዉቃል ማለት ነዉ። ያለዉን የጽጥታ ሁኔታ በደንብ ያዉቃል ማለት ነዉ። አሜሪካኖች የራሳቸዉ የግል ፍላጎቶችም ይኑራቸዉ ወይ ላለዉ ችግር መፍትሔ ለመስጠት ፍላጎት ይኖራቸዉ ብቻ የሆነዉ ይሁን በሁለት አምባሳደሮች ደረጃ ነበር ከኛ ጋር በስፍራዉ የነበሩት። ይኼ ሰዉ እንደዛ ነዉ ምላሽ የሰጣቸዉ።

ከዚያ በዃላ በግድ ነዉ አምጥተዉ አጠገባችን ያስቀመጡኣቸዉ:: አንድ ምሽት ወደ አስራ አንድ ሰኣት አከባቢ ተገናኝተን ማቅረብ የነበረብንን ማለትም እንዴት IRR በስራ ላይ እንደሚዉል የያዝነዉን ሮድማፕ ማቅረብ ስንጀምር በመካከላችን የነበሩት አምባሳደሮችና ታዛቢዎች ያገናኙን ወገኖች ይኼ ዉይይት እንዳይቋረጥ መፍትሔ ላይም እንዲደረስ ይህም ግንኙነት በክፉ ድባብ መለያየት እንዳይመጣ ትልቅ ፍላጎት አሳይተዉ ነበር። በነገሮች ስምምነት ላይ መድረስ እንኳን ባትችሉ ህዝብ ትልቅ ችግር ዉስጥ ነዉ ያለዉና ለህዝባችሁ አስቡ በበሽታና በራሃብ እየተሰቃየ ስለሆነ እርዳታ እንድንናደርስላችሁ ለሰብአዊ እርዳታ የተኩስ ማቆም ስምምነት እንኳን አድርጉ ያሉበት ደረጃም ነበር። ይኼ የሰላም ድርድሩ እንኳን መቀጠል ባይችል የተኩስ ማቆሙን ድርድር እንኳን እናድርግ ብለን ተገናኘን። ነገር ግን ለዚህ ተገናኝተን ለአምስት ደቂቃ እንኳን አብረዉን ሊቆዩ አልቻሉም።

‘ህገ-መንግስቱ አይፈቅድም እናንተ ሀገር ልታፈርሱ ነዉ፣ በዚህ ከእናንተ ከተሰማማን ደግሞ ፋኖም ነገ ይኼንኑ ይጠይቀናል ይህንንም ደግሞ ይፋ ልናድርግ የምንችልበትም መንገድም የለንም’

ወዘተ ብለዉ ከድርድሩ ወጥተዉ ሄዱ። ያዉ እንደለመዱት ተሰባስበዉ በሆቴላቸዉ ተከተዉ ቁጭ ይላሉና መልሰን መገናኘታችን አይቀርም ብለን አምባሳደሮቹም ከኛዉ ጋር ቁጭ ብለዉ እየጠበቅን በነበረበት ሁኔታ ዉስጥ ያ ሬድዋን ሁሴን የተባለዉ ሰዉዬ በተንሻፈፈ ስድብ በሚመስል ኢንጊሊዚኛዉ በቲዊተር ገጹ ላይ ያሰፈረዉ ጽሁፍ ሁሉን ነገር እንዲቋረጥ አደረገ ማለት ነዉ።

እንጊዲህ በታንዛንያ የነበረዉ የሰላም ድርድር ሂደት ይህንን ይመስል ነበር። ከዚያ በዃላ ወዲያዉኑ ከዚያዉ ምሽት ጀምረዉ ከዚያ ሸሽተዉ ሄዱ። እነሱ አቋርጠዉ ሸሽተዉ ስለሄዱ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር – የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ለብቻዉ ማድረግ የሚችለዉ ስላልነበረ ለእርቅ ሲባል ደግሞ መሰዋዕትነትም ቢሆን ለእርቅ ስንል ነብሳችንንም እንሰዋለን ብለን የኦሮሞ ህዝብ ይለፍለት እንጂ እኛ ብንሰዋም ሞትን አንፈራም ብለን አምባገኑ መንግስት በሚቆጣጠረዉ የአየር ክልል የኢትዮጵያ የአየር ክልል ዉስጥ ነዉ አልፈን እዚያ የሄድነዉ:: ጓዶች ነብሳቸዉን ለአደጋ አጋልጠዉ መሞት በጠመንጃ ብቻ አይደለም መሰዋት በጦር ሜዳ ላይ ብቻ አይደለም፣ ለህዝባችን እስከሆነ ድረስ ሰላምን እስካመጣ ድረስ መሰዋትን አንፈራም ብለን ሄድን ከዚያ በላይ ማድረግ የምንችለዉ እጅ መስጠት ብቻ ካልሆነ በስተቀር ምንም አልነበረም:: እጅ መስጠት ደግሞ በፍጹም የማይታሰብ ስለሆነ፤ በዘመናት መካከል የኦሮሞ ህዝብ ዉድ ልጆቹን የሰዋበትን የነጻነት ትግል፣ ብዙ ሺዎች የተሰዉበትን የነጻነት ትግል፣ ተላላቆቻችን እንኳን ዛሬ ድረስ የተዋረዱበትን፣ ለሰላም ብለዉ ከአስመራ ከተመለሱበት እለት ጀምሮ ብዙዎቹ ዛሬ እስር ቤት ናቸዉ፣ ሌሎቹ ደግሞ የህይወት መስዋዕትነት እየከፈሉ ነዉ፣ ሌላዉ ደግሞ በቤቱ ዉስጥ ቢያንስ ቢያንስ አምላካቸዉ የሰጣቸዉን ንጹህ አየር ከላያቸዉ ላይ አልቆረጡም እንጂ ይኼ አምባገነናዊ መንግስት ሌላዉን ሁሉ ከላያቸዉ ላይ ቆርጦ ባሉበት ሁኔታ ዉስጥ፤ እጅ መስጠት የሚባል ነገር የሚታሰብም ስላልሆነ የሚገባም ስላልነበረ የትጥቅ ትግላችን አሁንም ለሌላ ዙር በሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ አተኮርን። የትጥቅ ትግል ደግሞ የሰዉን ነብስ ነዉ የሚያጠፋዉ፣ የሀገር ሃብት ንብረት ነዉ የሚያጠፋዉ፣ ቤተሰብን ነዉ የሚበትነዉ፣ መሬትን ነዉ የሚያራቁተዉ፣ የሰዉ ልጅ ህይወትና ኑሮ ነዉ የሚያጎሳቁለዉ፤ ያ አምባገነናዊ መንግስት ደግሞ ይህ እንዲቀጥል ነዉ ከድርድሩ ሸሽቶን የሄደዉ። ያንን የሬድዋንን ስድብ እዛዉ ክፍል ዉስጥ ቁጭ እንዳልን ከአምባሳደሮቹ ጋር ነዉ ያየነዉ። አምባሳደር ማይክ ሀመር ነበር በቅድሚያ ያየዉ; ያዉ በዚያ ላይ ተመስርተን ነበር የተነጋገርነዉና በድርድሩ ተስፋ መቁረጥ የመጣዉ።

በሰብአዊ እርዳታ ማድረስ ላይ ተመስርቶ ለአንድ ሳምንትም ይሁን ለሁለት ሳምንታት ተኩስ ማቆም ስምምነት እንኳን ሳይሳካ ቀረ። ይኼ መንግስት የፈረመዉ ግዴታ ነበረዉ; ነገር ግን እንደ ህጻን ሸሽቶ ሄደ፣ በመካከላችን የነበሩት ICRCን ጨምሮ እኛም ወደ ሀገር በምንመለስበትና ከዚህም በዃላ ተመልሰን የሚንገናኝበት እድልን አስመልክቶ ከዚህም በፊት ያዉ ጥርጣሬ በመካከላችሁ ነበር እንደዛ ኣይነትም ጥርጣሬ መንግስት ይኼን አክብሮ ከፈጸመ እንኳን በትንሹ ጥርጣሬዉ ይቀንስ ይሆናል ተብሎ ተስፋ ተደርጎበት የነበረ ቢሆንም አምባገነናዊ መንግስት ግን በጥርጣሬ ላይ ሌላ ጥርጣሬ ጨመረ።

‘የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት የአለም አቀፍ ህጎችን አያዉቅም’ ብለዉ የነበሩት የአለም አቀፉን ህጎች ይቅርና እዚያው የፈረሙትን ፕሮቶኮል እንኳን ማክበር አቃታቸዉ:: ያንን እንኳን አያዉቁም ያንንም ሸሽተዉ ወደ ሀገር የምንመለስበትን በቅድሚያ ተፈርሞ የነበረን ዉል እንኳን እምቢ አሉ። እነሱ ያንን እምቢ ሲሉም እኛ መለማመጥም አልሄድንም:: ጊዜ ወሰድን፣ በዚያም እድል ተጠቅመን እንደሆነ ብዙ መንግስታት ኢንቨስት ያደረጉበት ጉዳይ ላይ ተሳትፈን ከኛ የሚፈለገዉን አድርገናል ብለን በፕሮቶኮሉ መሰረት መሄድን ይሄ መንግስት እምቢ ስላለ እኛ የተወሰነ ጊዜ ወስደን የምንሰራቸዉ ስራዎቹም ነበሩን:: እነዚያን ስራዎች ሰርተን፣ መቅረፍ የነበሩብንን ችግሮች ቀርፈን፣ የወደፊት አቅጣጫዎችን ተለዋዉጠን፣ መጀመርያዉኑ ባስተካከልነዉ መንገድ ላይ ተመልሰን ገባን ማለት ነዉ።

ዬትኛው መንግስት አለና ነዉ ዬትኛዋ ኢትዮጵያ አለችና ነዉ ድንበርዋ ከሰሜን እስከ ደቡብ ተጠብቆ የሚያስቸግረዉ? ምንም የሚያስቸግር አልነበረም። መንግስት ድንበሩን መጠበቅ ይቅርና የመኖርያ ቤቱን አከባቢ ራሱ መጠበቅ ያልቻለ መንግስት ነዉና ያለዉ ተመልሶ ወደ ሀገራችን መግባት ምንም የሚያስቸግር ነገር የለም ብለን አምነንበት ነዉና የወጣነዉ አስተካክለን አስበንበት የወጣነዉ ስለነበረ በዚያዉ መንገድ ወደ ትግል ሜዳችን ተመለስን ማለት ነዉ። እንጊዲህ የድርድሩ ጉዳይ ይህንን ይመስላል።»

ትርጉም በፀጋዬ ኃይሉ ባልቻ ሚያዚያ 22, 2024 ኖርዌይ

Leave a Reply

Discover more from Qeerroo Bilisummaa Oromoo

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading