• Sat. Nov 21st, 2026

ከኢትዮጵያ ሕዝባዊ ኃይሎች ትብብር ለሕልውና (ትብብር ለሕልውና) ምክር ቤት የተሰጠ መግለጫ

Oct 31, 2026

የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ኃይሎች ትብብር ለሕልውና ምክር ቤት ስድስተኛ መደበኛ ስብሰባውን ከጥቅምት 20 እስከ 21/ 2019 ዓ.ም አካሂዷል። ምክር ቤቱ የትብብሩ መመስረት በይፋ ከታወጀ በኋላ ባካሄደው በዚህ የመጀመርያ ስብሰባ ወቅታዊ ዓለም አቀፋዊ፣ ቀጣናዊ እና ሀገራዊ የኃይል አሰላለፍ ሁኔታዎችን እንዲሁም የኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ተጨባጭ ሁኔታ በጥልቀት በመገምገም የትብብሩን የመካከለኛ ጊዜ ዕቅድ ያፀደቀ ሲሆን በሌሎች ልዩ ልዩ አጀንዳዎችም ላይ ተወያይቷል።

በምክር ቤቱ ግምገማ መሰረት ኢትዮጵያ በአምባገነናዊ ዘረ-ፈጅ አገዛዝ ስር የወደቀች፣ የዜጎች መፈናቀል እንዲሁም የከፋ ድህነትን መገለጫዋ ያደረገች ሀገር ሆናለች። በትግራይ፣ በአማራ፤ በኦሮሚያ እና  በሌሎች ሕዝቦች ላይ በይፋ ባወጀው ጦርነት ምክንያት ዜጎች እንደሰው የመኖር ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብታቸው የተገፈፈ እንዲሁም እንደሕዝብ የመኖር ሕልውናቸው አደጋ ውስጥ የወደቀ ሆኗል። በተጨማሪም በሕዝቦች መሃል የእርስ በርስ ግጭቶችን በመፍጠር በሞያሌ፣ በአርሲ፣ በወለጋ፣ በጋምቤላ፣ በሱማሊ፣ በአፋር፣ በሲዳማና በሌሎች አከባቢዎች እንደታየው ሞት፣ እልቂትና ከፍተኛ ውድመትን በመፍጠር ዘረ-ፈጁ አገዛዝ የሕዝቦች የህልውናና የደህንነት ጠንቅ ሆኖ ቀጥሏል።

አገዛዙ ሀገሪቱንና ሕዝቦቿን እየበላ ያለውን ጦርነት የመግታት፣ ዘላቂ ሰላም የማምጣት፣ የዜጎችን ፍላጎት  የማድመጥና የማረጋገጥ፣ ሕግና ሥርዓትን የማስፈን፣ ድህነትንና ኋላቀርነትን እንዲሁም ዘርፈ ብዙ ሀገራዊ ችግሮችን የመፍታት ባህሪ፣ አቅምና ፍላጎት ስለሌለው ውስጣዊ ችግሮችን ለመደበቅ በአይዞህ ባዮቹና በላኪዎቹ ፍላጎት መሰረት በሀገር ውስጥ የቀሰቀሳቸውን ጦርነቶች በማስፋት ቀጠናዊ ጦርነት ለማድረግ የጎረቤት ሀገራትን መውጋትና መተንኮስን ተያይዞታል። ይህም የሀገሪቱንና የሕዝቦቿን ሕልውና ከድጡ ወደማጡ የሚከት፣ የቀጠናውን ሀገራት ሰላምና እድገት የሚያውክ፣ የዓለም አቀፍ ማህበረሰቡንም ጥቅም አደጋ ላይ የሚጥል አካሄድ ነው።

የትብብሩ ምክር ቤት ሰፊና ጥልቅ ወቅታዊ ግምገማ ካካሄደ በኋላ የሚከተሉትን መሰረታዊ መርሆዎችን አጽንቷል።
1.⁠ ⁠የብልጽግና አገዛዝ ለሕዝቦች ሰላምና ደህንነት፣ ማሕበራዊ ውልና ባህላዊ መሰረት፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በፍጹም ግድ የሌለው የሀገርንና የሕዝቦችን ሕልውና አደጋ ውስጥ በመክተት የስልጣን ዕድሜውን ማራዘም የሚፈልግ አገዛዝ ነው። ስለሆነም በስልጣን ላይ ያለው አምባገነናዊ ዘረ-ፈጅ አገዛዝ የሁሉም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ጠላት ነው።
2.⁠ ⁠የትብብር ለህልውና መሰረታዊ ዓላማ የብልጽግናን አምባገነናዊ ዘረ-ፈጅ አገዛዝ ከስልጣን በማስወገድ ላይ የተገደበ ትብብር ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ሕዝቦች ህልውና ለማረጋገጥ የተመሰረተ ስትራተጂካዊ ትብብር ነው። ትብብር ለህልውና ኢትዮጵያን ለዘመናት ተብትቦ የያዛትን የጦርነት አዙሪት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መስበር የሕዝቦችን ፍላጎት መሰረት ያደረገ ሁሉን አቀፍ የሽግግር ምዕራፍ መክፈት ጽኑ አቋሙ ነው። ይህ ታሪካዊ ተልዕኮም በትብብር ለህልውና ብቻ የሚፈጸም እንዳልሆነ ግልጽ ነው። በሽግግሩ ሂደት የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማሕበራትና የልዩ ልዩ ሕዝባዊ ተቋማት እንዲሁም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ንቁና ቀጥተኛ ተሳትፎ መተኪያ የሌለውና ወሳኝ ጉዳያችን መሆኑን እናረጋግጣለን።
3.⁠ ⁠የአፍሪካ ቀንድ ሰላም፣ ልማትና ትብብር የኢትዮጵያ የመጪው ዘመን የፖለቲካ፣ የማህበረ-ኢኮኖሚና የዲፕሎማሲ ምሰሶዎችን የሚያጠናክር መሆኑን ትብብር ለህልውና ያምናል። ይህንን ወሳኝ ጉዳይ ተግባራዊ ለማድረግ ትብብሩ በቀጠናችን ሕዝቦችና ሀገራት መካከል የኖረውን የጋራ መግባባትንና አብሮነትን ለማስፈንና ወዳጅነትን ለማጠናከር ካለመታከት ይሰራል።

የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በግልፅ በመረዳት፣ ባስቀመጣቸው መርሆች በመመራትና ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት የትብብሩ ምክር ቤት የሚከተለውን የመካከለኛ ጊዜ የተግባራት ዕቅድ አጽድቋል።
1.⁠ ⁠ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ሕልውና የሚያካሄደውን ዘርፈ-ብዙ ትግል ማጠናከር፤
2.⁠ ⁠በሀገር ውስጥና በዲያስፖራው ማህበረሰብ የሚካሄደውን ህዝባዊና ዲፕሎማሲያዊ ትግል ማበረታታትና ማቀናጀት፤
3.⁠ ⁠የትብብር ለህልውና አባል ድርጅቶችን አቅም ማጠናከርና በአገዛዙ ላይ ውጤታማና ተግባራዊ እርምጃዎችን መውሰድ፤
4.⁠ ⁠የትብብሩን ዓላማና ግብ ለማሳካት ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሲቪክ ማሕበራትና ልዩ ልዩ ሕዝባዊ ተቋማት እንዲሁም ከትብብሩ ዓላማ ጋር ከቆሙ ምሁራንና ዲፕሎማቶች እንዲሁም ተሰሚነት ካላቸው እውቅ ግለሰቦች ጋር በቅርበት መስራት፤
5.⁠ ⁠ከአፍሪካ ቀንድ ሕዝቦችና መንግስታት ጋር ወዳጅነትና ትብብርን ማጠናከር፤
6.⁠ ⁠የዲፕሎማሲና የሚድያ ሥራዎችን ማጠናከር፤
ከዘህ በመነሳት የትብብር ለሕልውና ምክር ቤት የሚከተሉት ጥሪዎች ያስተላልፋል፤

ለመላው ህዝቦቻችን

የብልጽግና አምባገነናዊ ዘረ ፈጅ-አገዛዝ ዋና ዓላማ ተፈጥሯዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችህን በመቀማት፣ ሕልውናህን አደጋ ውስጥ በመክተት፣ የሀገርንና የህዝብን ጥቅም በመሸጥ በስልጣን የመቆየትና የላኪዎቹን ፍላጎት ማሳካት ነው። ስለሆነም ከህዝባዊ ኃይሎች ጋር በመሆን እያደረግክ ያለኸውን ትግል አጠናክረህ እንድትቀጥል ጥሪያችንን እናቀርባለን።

ለመላው የትብብር ለሕልውና አባል ድርጅቶች

የህዝቦቻችንን የሕልውና አደጋ የመቀልበስ፣ በኢትዮጵያውያን መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ የሽግግር ምዕራፍ የመከፈት፣ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት የመገንባት ሥራዎች የሚወሰኑት ሰራዊታችን በሚከፍለው የማይተካ መስዋዕትነት ነው። በመሆኑም የየድርጅቶቻችን ሰራዊት እርስ በርስ በመተሳሰር በጋራና በአንድነት የጠላትን አከርካሪ በመስበር የአገሪቱንና የህዝቦችዋን ሕልውናና ሰላም ለማረጋገጥ ከመቸውም ጊዜ በላይ ተግተንና ተናበን በመሥራት ታሪካዊ ኃላፊነታችንን በተግባር እንደምንወጣና የድል ባለቤቶች እንደምንሆን እናረጋግጣለን።

ለቀጠናውና ለዓለም አቀፍ ማሕበረሰብ

መላው የዓለም ዓቀፍ ማሕበረሰብ የብልፅግና አምባገነናዊ ዘረ ፈጅ አገዛዝ በቀጠናው ጦር ሰባቂና ግጭት ጠማቂ በመሆን በሀገሪቱ ህዝቦችም ሆነ በአከባቢው አገራት የሕልውናና የሰላም ደህንነት ጠንቅ በመሆን እየተጫወተ ላለው አፍራሽ ሚና በተገቢው መንገድ በመረዳትና ከትብብር ለሕልውና ኃይሎች ጋር በመተባበር የኢትዮጵያ ህዝቦች ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩና በቀጠናው ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር ለማድረግ እንዲሰራ ስንል ጥሪያችንን እናቀርባለን።

የኢትዮጵያ ህዝባዊ ሃይሎች ትብብር ለህልውና (ትብብር ለህልውና) ምክር ቤት

ጥቅምት 21, 2019 E.C.
#Oromia #Ethiopia

Leave a Reply