መጋቢት 23, 2026 ባወጣነው መግለጫ፣ አብይ አህመድ በቀጣይ ወራት ሊጫወታቸው ያዘጋጃቸው የማጭበርበሪያ ካርዶችን ዘርዝረን ነበር። ብዙዎቹን አልፈን አሁን በብሔራዊ ሞኖሎግ አማካኝነት “ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ” ተብዬ ማጭበርበሪያው ላይ ደርሰናል። ጥቂት ተጨማሪ ነጥቦች፡-
1. ይህ ሞኖሎግ በአብይ አህመድ እና በራሱ ነጸብራቅ መካከል የሚደረግ ከንቱ ተግባር እንደሆነ በዋና ዋና የፖለቲካ ተዋናዮች መካከል መግባባት አለ። ሞኖሎጉ ላይ፣ የተቃውሞም ሆነ ገለልተኛ ድምጾች እንዲሁም ህጋዊ የህዝብ ተወካዮች እንደሌሉበት የተቋቋመ ሃቅ ነው።
2. መድረኩ ከጅምሩ አካታች እና ገለልተኛ ሆኖ የተገነባ ቢሆን እንኳን፣ በአብይ አህመድ አገዛዝ ስር እውነተኛ ብሔራዊ ውይይት ሊኖር አይችልም። የዚህ መድረክ ውጤት ምንም ይሁን ምን፣ መዳረሻው የአብይ አህመድ ጠረጴዛ ነው። ያለፉት ስምንት መራራ ዓመታት አንድ ነገር ካስተማረን፣ አብይ አህመድ ለየትኛውም የማህበረሰብ ጥያቄ ወይም ፍላጎት ሊታመን እንደማይችል ነው። መነሻውም መዳረሻውም ምን እንደሚያደርግበት የማያውቀው የፖለቲካ ስልጣን ነው።
3. በሞኖሎጉ ቀረቡ የተባሉ የሕዝብ ጥያቄዎች፣ ሁለት ዓላማዎች ለማሳካት ነው፡፡ ወደ ሁለት ጊዜ የፕሬዚዳንትነት ጉዞ መንገድ ለመጥረግ እና የኦሮሚያ፣ የአማራ እና የሌሎች የክልል መንግስታትን ወደ ትንንሽ ግዛቶች በመሸርሸር፣ በየክልሉ የጎላ የአከባቢያዊ ማንነት ልዩነትን ወደ መንግስታዊ እና ፖለትካዊ ልዩነቶች ለማሸጋገር ነው። ይህም በየክልሉ እየተያያዘ ሃገራዊ ቅርጽ መያዝ የጀመረውን ጸረ አገዛዝ ትግል መሠረቱን ከስር ለማዳከም ነው።
4. የሕዝብ መሠረታዊ እና መዋቅራዊ ጥያቄዎች ሁሉን አቀፍ ውይይት ይጠይቃሉ። ይህም ከአብይ መወገድ ማግስት፣ ጦርነት በሌለበት እና ለውይይት በተመቸ ዐውድ ውስጥ ብቻ የሚሳካ ነው።
5. ለዚህ የፖለቲካ ወንጀል የተባበሩ ኮሚሽነሮች እና ሌሎች ፈቃደኛ ተባባሪዎች፣ ይህ የአንድ ወገን ትዕይንት መሆኑን እና መሰረታዊ የሃገረ መንግስቱን ማነቆዎች እንደማይፈታ በሚገባ እያወቁ በወንጀሉ ዉስጥ ተሳታፊ የሆኑ አካላት ህጋዊ እና ታሪካዊ ኃላፊነት ይጠብቃቸዋል።
የኦነግ-ኦነሳ ከፍተኛ ዕዝ
ሐምሌ 19, 2026

